የተፈጥሮ አካባቢን መንከባከብና የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ከዓለም አቀፍ አጀንዳነቱ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶች ላይ አዲስ ምዕራፍ እየከፈተ ይገኛል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በሀገራዊ ጥሪ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፣ ዛሬ በቀላሉ ዛፍ የመትከል ዘመቻ መሆኑ አብቅቶ የሕዝባዊ ባህል አካል እና የብሔራዊ መግባባት ትልቅ መድረክ ለመሆን በቅቷል።
ይህ በየዓመቱ የሚካሄደው መርሐ ግብር በመላው ኢትዮጵያ አዲስ የማኅበረሰብ እንቅስቃሴን የፈጠረ ሲሆን፣ ዕድሜ፣ ጾታ፣ የትምህርት ደረጃ እና የኑሮ ሁኔታ ሳይለያያቸው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጋራ ዓላማ እንዲሰለፉ አድርጓቸዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ የሚተከለው ችግኝ "ሀገር የጋራችን ናት" የሚለውን እውነት በተግባር ያሳያል።
ከአንድ ክልል የተዘጋጁ ችግኞች ወደ ሌላ ክልል እየተጓጓዙ ሲተከሉም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እና ወንድማማችነትን ይበልጥ ያጠናክራሉ።
የአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት በሚተከሉት ችግኞች ብዛት ብቻ ሳይሆን በሚሰጠው ዘላቂ ጥቅምም ይለካል።
የአፈር መሸርሸርን በመከላከልና የውሃ ሀብትን በማደስ ለግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ ዋስትና እየሆነ ይገኛል።
በተጨማሪም የፍራፍሬ እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በመተከላቸው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ገቢ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።
መርሐ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ አልፎ የሀገራዊ አንድነትና የሕዝቦች አዎንታዊ ግንኙነት መገለጫ ሆኗል።
የተተከሉት ችግኞች ጸድቀው ለፍሬ እንዲበቁ ማድረግ የሁላችንም ዘላቂ ኃላፊነት ሲሆን፣ ሀገር በልማት፤ ማኅበረሰብ ደግሞ በመግባባትና በአንድነት አረንጓዴ ሆኖ ይበቅላል።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: