Search

የአርቲስት ደበበ እሸቱ አስከሬን የክብር ሽኝት መርሐ ግብር እየተከናወነ ይገኛል

ማክሰኞ ነሐሴ 13, 2017 174

የአርቲስት ደበበ እሸቱ አስከሬን የክብር ሽኝት መርሐ ግብር በብሔራዊ ቴአትር እየተካሄደ ይገኛል።

በሽኝት መርሐ ግብሩ የአርቲስት ደበበ እሸቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች እና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት ነው እየተከናወነ የሚገኘው።

በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የሁለገቡ አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥራዎችን የሚያሳይ ዶክመንተሪ የታየ ሲሆን፤ የሙያ አጋሮቹ በሕይወት ዘመኑ ያበረከታቸውን ስራዎች በትውስታ አንስትዋል።

የባህልና ስፖርት ሚንስትሯ ሸዊት ሻንካ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ሁለገቡ አርቲስት ደበበ እሸቱ ከኪነጥበቡ ባሻገር፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴም ጉልህ ተሳትፎ ያለው ዘርፈ ብዙ ባለሙያ ነበር ብለዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ለሀገራቸው ያላቸውን የማይናወጥ ፍቅር እስከ እስትንፋሳቸው መጨረሻ ያሳዩ ፅኑ ሀገር ወዳድ ነበሩ።

የታሪክ ድርሳናቸው እንደሚያስረዳው አርቲስት ደበበ እሸቱ 1933 . ነው የተወለዱት። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ እያሉ ቲያትር የመስራት ዕድሉ ገጥሟቸው ነበር።

ከዛ በመቀጠል የአብራሪነት ስልጠና ለመውሰድ እጩ መኮንን ሆነው የኢትዮጲያ አየር ሀይልን ተቀላቀሉ። በአየር ኃይል የመዝናኛ ክፍሉ ላይ በመሳተፍ ቲያትር ሰርተዋል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ፤ በሀገር ፍቅርና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (የአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) መድረክ ላይ ለረዥም ዓመታት በተዋናይነትና በአዘጋጅነት አገልግለዋል።

በተለያዩ ፊልሞች ላይ በመሪ ተዋናይነትም ተሳትፈዋል። በሆሊውድ በተሠራው 'ሻፍት ኢን አፍሪካ' በተሰኘው ፊልም ላይ በመሳተፍም ስማቸውን በደማቁ ፅፈዋል።

በእንግሊዘኛ ከሠሩባቸው ፊልሞች መካከል ' ሴይለር ፍሮም ጂብራልታር' 'ጉማ' ' አፍሪካን ስፓይ' 'ዜልዳ' ' ግሬቭ ዲገር' እና ' ግሬት ሪቤሊየን ' ይጠቀሳሉ።

' ጌም ኦፍ ቼዝ' ላይ በትወና 'ኦቴሎ' ላይ በመተወን እና በማዘጋጀትም የጥበብ አሻራቸውን አኑረዋል።

ደበበ እሸቱ ከአርቲስቱ በተጨማሪ በራድዮና በቴሌቪዥን ሥራዎችም ላይ ተሳትፈዋል። 'ያላቻ ጋብቻ' 'ሮሚዎና ዡልየት' እና 'ዳንዴው ጨቡዴ' ከተወኑባቸው ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

አርቲስት ደበበ እሸቱ በአውሮፓውያኑ 1985 ዚምባቡዌ በተካሄደው ቴአትር ለልማትና ዕድገት ወርክሾፕ ላይ በብቃት በመሳተፍ የአፍሪካ የመድረክ ባለሙያዎች ማሕበርን አስተባብረው በማቋቋም የማሕበሩም መስራች ፕሬዚዳንት ሆነው 12 ዓመታት አገልግለዋል፡፡

ለአፍሪካ ቲያትር ባደረጉት አስተዋጽኦ የዚምባብዌን ማላካይት አዋርድ ወስደዋል። ጣይቱ ኢንተርቴንመንት በዋሽንግተን ዲሲ በቲያትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡

በአትላንታ ጂኦርጂያ የከተማው ምክር ቤት ለዓለም ቲያትር ባደረጉት አስተዋጽኦ ኖቬምበር 24 የደበበ እሸቱ ቀን በሚል ሰይሞላቸዋል፡፡

የኢትዮጲያ ባህል ሚኒስትርም ለኢትዮጲያ ፊልም እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሸልሟቸዋል፡፡

በጉማ አዋርድም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በአውሮፓውያኑ 2015 በቫንኮቨር ዓለማቀፍ ፊልም ፌስቲቫልም በምርጥ መሪ ተዋናይ ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ 2015 . አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሃገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሸልሟቸዋል።

በዘአማኑኤል መንግስቱ