የአንድ ሀገር የመከላከያ ሠራዊት ጥንካሬ ሲነሳ ከታጠቀው የጦር መሣሪያ ብዛት ወይም ከሰው ኃይል ቁጥር ብቻ ተነጥሎ አይታይም።
እውነተኛው፣ አስተማማኙ እና የማይበገረው የሠራዊት ጥንካሬ የሚመነጨው ከአባላቱ የአእምሮ ብቃት፣ ከዕውቀት ደረጃቸው እና ከላቀ የስትራቴጂያዊ አስተሳሰባቸው ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታትየኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ታሪካዊ እና አኩሪ ጀግንነቱን ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማዋሃድ ትምህርት እና ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ሥር ነቀል ተቋማዊ ግንባታን አከናውኗል።
ዛሬ ላይ መከላከያ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የተለያዩ ወታደራዊ የትምህርት ተቋማት የሠራዊት አባላትን በዘመናዊ ዕውቀት እና ክህሎት እያነፁ ተቋሙን የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ምሽግ አድርገውታል።
የዘመናችን ጦርነት የሚካሄደው በርካታ ሠራዊት በማሰማራት በግንባር ላይ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ በኢኮኖሚ፣ በመረጃ እና በሳይበር አውታሮች ጭምር ነው።
ይህንን ውስብስብ የዘመኑን እውነት የተረዳው ሠራዊታችን ከጊዜው ጋር የሚራመድ የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል።
ይህ አዲስ ገጽታ ደግሞ ወታደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጠለቀ የአእምሮ ብቃት እና ዕውቀት እንዲኖረው አስችሎታል።
የጦር ኃይሎች ተቋማት ወታደሩ የዘመናዊ ጦርነትን ተለዋዋጭ ባሕርይ እንዲገነዘብ፣ የስትራቴጂያዊ አስተሳሰብ ክህሎቱን እንዲያዳብር፣ እንዲሁም በሳይበር ደኅንነት፣ በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ የመገናኛ መረቦች የተካነ እንዲሆን ሰፊ ሥራ እየሠሩ ነው።
የመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ፣ የመከላከያ ዋር ኮሌጅ፣ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ እና ሌሎችም አካዳሚዎች ከፍተኛ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ የሠራዊቱን አባላት በምሁርነት ደረጃ እያነፁ ይገኛሉ።
በተለይም የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን እና አመራሮችን በሀገር አቀፍ የደኅንነት ስትራቴጂዎች ላይ ሲያሰለጥን፣ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ደግሞ ሠራዊቱን በኢንጂነሪንግ ዘርፍ በማብቃት ለኢትዮጵያ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ለጦር መሳሪያዎች ፈጠራና ጥገና የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በተጨማሪም የመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ወታደሩን በስትራቴጂያዊ ዕቅድ እና አመራር ጥበብ በማሰልጠን በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ብቁ፣ ፈጣን እና አሸናፊ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ የሚችል የላቀ አመራር እየፈጠረ ነው።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የትምህርት ተቋማቱን የላቀ የዕውቀት ማዕከል አድርጓቸዋል።
እነዚህ ተቋማት ወታደሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በፅኑ መሠረት ላይ እንዲጠብቅ የሚያስፈልገውን ዕውቀት እና ክህሎት እንዲታጠቅ እያደረጉት ነው።
ይህ የዕውቀት እና የጀግንነት ውህደት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ታላቅ ኩራት የሚሰጥ እና ማንም የማይደፍረው አስተማማኝ የመከላከያ አቅም ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: