Search

ትዴፓ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን አደነቀ፤ ለትግራይ ወጣቶችም የድጋፍ ጥሪ አቀረበ

እሑድ ነሐሴ 10, 2018 73

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) በሀገራችን እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህል እና የመደጋገፍ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ገለጸ።

ፓርቲው በወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታ እና በወጣቶች ዕጣ ፈንታ ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የትግራይ ሕዝብ ድምፅ እና እውነተኛ ፍላጎት በሀገራዊ መድረኩ ላይ እንዲደመጥ ከአጀንዳ ማሰባሰብ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር በቅርበት ሲሠራ መቆየቱን የገለጸው ፓርቲው፣ በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተመረጡ 300 በላይ የትግራይ ሕዝብ ተወካዮች በሂደቱ በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን አስታውቋል።

ይህ የምክክር ሂደት ልዩነቶችን በኃይል የመፍታት ጎጂ ልማድን በማስቀረት፣ በሠለጠነ መንገድ በመደማመጥ እና በውይይት መፍትሔ የመፈለግ አዲስ ባህል እንዲፈጠር ማድረጉን ትዴፓ አድንቋል።

ሂደቱ ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎችን በማከም ለዘላቂ ሰላም እና ልማት መንገድ የሚከፍት መሆኑንም አመላክቷል።

ፓርቲው አሁናዊውን የትግራይ ሁኔታ እና የወጣቶች እጣ ፈንታን በተመለከተ ባስተላለፈው የሰላም እና የትብብር ጥሪ፣ ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን አሁንም ድረስ በሚያካሂደው የጦርነት ዜማ ምክንያት በወጣቶች ሕይወት እና የነገ ተስፋ ላይ እየደረሰ ባለው መደናቀፍ በእጅጉ ማዘኑን ገልጿል።

የወጣቶች ቦታ የትምህርት ገበታ፣ የምርምር ማዕከል እና የልማት ሜዳ እንጂ የጦር ግንባር ባለመሆኑ፣ ወጣቱ ትውልድ ራሱን ከጦርነት እና ከጥፋት አውድ ነፃ የሚያወጣበትን አቅጣጫ መከተል እንዳለበት አሳስቧል።

ራሳቸውን ከግጭት ስጋት ለማዳን ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች አካባቢዎች በመምጣት በከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንግልት ውስጥ ለሚገኙ የትግራይ ወጣቶች የመንግሥት አካላት፣ ባለሀብቶች እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ትዴፓ ጥሪ አቅርቧል።

ወጣቶቹ ሠርተው ራሳቸውን እንዲደግፉ ጊዜያዊ እና ዘላቂ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ወንድማማችነትን ማሳየት እንደሚገባም በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።

በወይንሸት ደጀኔ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: