የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ በቀን 60 ሺህ ሜትር ኪዩብ ንፁህ የመጠጥ ውኃ የሚያመርት እና በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የሚያጣራ የኮዬ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክት፣ የከተማዋን ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሳደግ በቱሉ ጉዶ፣ ለገዳዲ ክፍል ሁለት፣ በረከት የጋራ መኖሪያ አካባቢ፣ ቦሌ አራብሳ እና በሌሎችም አካባቢዎች በርካታ የውኃ ጉድጓዶች መለማታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በከተማዋ ከአምስት ዓመት በፊት በቀን 525 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብቻ የነበረውን የውኃ ማምረት አቅም በአሁኑ ወቅት በቀን ወደ 910 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።
በተመሳሳይ ለረጅም ዘመናት በአዲስ አበባ የሚገኙ ወንዞች በፍሳሽ እና በደረቅ ቆሻሻ ሲበከሉ መቆየታቸውን ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች፣ ይህንን ችግር ለመፍታት የፍሳሽ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት የከተማዋን የማጣራት አቅም ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
ከለውጡ ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት፣ በ2009 ዓ.ም በቀን 20 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብቻ የነበረው የፍሳሽ ማጣራት አቅም የዛሬውን ፕሮጀክት ጨምሮ ከ253 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ መድረሱን አስገንዝበዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን ጤና እና ንፅህና ከመጠበቅ ባለፈ የወንዞችን ብክለት በመቀነስ እና የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
አዲስ አበባን ውብ፣ ጽዱ፣ ጤናማ፣ አረንጓዴ፣ ዘመናዊ እና ለትውልድ የምትመች ከተማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለፕሮጀክቱ መሳካት የብድር አገልግሎት ለሰጠው የዓለም ባንክ፣ የውኃ መገኛ አካባቢዎችን በትብብር ለማልማት ላገዘው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ለልማት ሲሉ መሬታቸውን ለለቀቁ አርሶ አደሮች፣ እንዲሁም ለውኃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን አመራሮች እና ባለሙያዎች በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: