ራስን እና ጠላትን በትክክል ማወቅ በመቶ ጦርነቶች እንኳን ላለመሸነፍ ቁልፍ መሆኑን የጦርነት ፍልስፍናዎች ያስተምራሉ።
በአሁኑ ውስብስብ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይህንን ጠላቶቹን በትክክል በማወቅ እና ከዘመኑ ጋር አቅሙን በማጎልበት፣ ቶሎ የመላመድ፣ የመማር እና አዳዲስ መፍትሔዎችን የመፍጠር ክህሎቱን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል።
የሀገር ሉዓላዊነት እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የሚለካው ሠራዊቱ በውጊያ አውድ ውስጥ በሚያሳየው ጦርነት የመቀልበስ አቅም እና በዘመቻ የበላይነት በመሆኑ ዘመናዊ የውጊያ ስልቶችን እና የላቀ የዘመቻ አመራርን የተላበሰ የቁርጥ ቀን ኃይል ሆኗል።
የሠራዊቱ የሎጂስቲክስ አቅም እና በየትኛውም የውጊያ ቀጣና ውስጥ ፈጣን የኃይል ስምሪት የማድረግ ብቃቱ፣ ሀገራዊ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እና መሠረተ ልማቶችን ከመጠበቅ የላቀ ተልዕኮ ጋር የተቆራኘ ነው።
ግዙፍ ኮሪደሮችም ሆኑ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በጥፋት ኃይሎች ዒላማ እንዳይሆኑ፣ መከላከያ ሠራዊታችን ጥልቅ በሆነ ወታደራዊ መረጃ፣ በቅድመ መከላከል የማጥቃት እርምጃ እና በከፍተኛ የውጊያ ስልት ለሴኮንድ ሳይዘናጋ ይጠባበቃል።
ይህ ጀግና ሠራዊት በማናቸውም አስቸጋሪ መልክዓ ምድር ውስጥ ጠላትን የማንበርከክ ብቃቱ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ጋር በጥብቅ የተዋሐደ ሲሆን የጠላትን የጥቃት ሞገዶች ከማምከንም አልፎ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን የበላይነት ያረጋገጠ ነው።
ከዚህም ባሻገር ይህ የማይበገር የውጊያ አቅም ወደ ማሪታይም ስትራቴጂ በመስፋፋት ላይ ነው። የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ዳግም መገንባት ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር እና ለአፍሪካ ቀንድ የባሕር ላይ ውጊያ ዝግጁ ያደርጋታል።
የዓለም ኃያላን ሀገራት በውኃ አካላት ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ፉክክር በሚያደርጉበት በዚህ ዘመን፣ ጠንካራ የባሕር ኃይል ማደራጀት ማናቸውንም የባሕር ላይ ስጋቶችን የመመከት እና የማጥቃት አቅም በመገንባት የሀገርን የውኃ ላይ ሉዓላዊነት በኃይል ጭምር ለማስከበር የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ክንድ ነው።
የወደፊቱ የባሕር ኃይላችን የኢትዮጵያን ወታደራዊ ተሰሚነት ከየብስ ወደ ባሕር በማሻገር የጠላትን ትንኮሳ በርቀት ለመቀልበስ የሚያስችል ቁልፍ የውጊያ አካል ይሆናል።
ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በተደረገው መሠረታዊ የሪፎርም ሥራ፣ ሠራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ እና የብሔር ወገንተኝነት የጸዳ፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ኃይል ሆኖ ዳግም ተገንብቷል።
በተለይም ልዩ የዘመቻ ኃይሎች፣ አየር ወለድ፣ ኮማንዶ፣ የሪፐብሊካን ጋርድ እንዲሁም ሌሎች የልዩ ኃይል ክፍሎች በላቀ ሥልጠና ተደራጅተው ውስብስብ ሀገራዊ ግዳጆችን እየፈጸሙ ነው።
ይህንን አስመልክቶ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት፣ የዘመኑ የጦርነት አካሄድ ከባህላዊው የሰው ኃይል እና የታንከኛ ውጊያ ተሻግሮ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ሠራዊታችን ይህንን ተረድቶ ራሱን በበቂ ቴክኖሎጂ አደራጅቷል።
ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግር የመከላከያ ኮሌጆች ዘመኑን የዋጀ ስትራቴጂያዊ የደኅንነት ትንተና በማካተት “ስማርት” ወታደራዊ አመራሮችን እንዲያፈሩ ከማድረጉም በላይ፣ የጠላትን ስትራቴጂካዊ ምሽግ ከርቀት ለማሽመድመድ ያስችላል።
የሠራዊታችን ሌላው ግዙፍ መገለጫ ዘመናዊ ትጥቁ ብቻ ሳይሆን እጅግ የላቀ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱ እና ወታደራዊ ዲስፕሊኑ ነው። ግዳጅን በሚፈጽምበት ወቅት የሕግ የበላይነትን እና የውጊያ ሕጎችን አጥብቆ የሚከተል ሲሆን የጠላትን ስብስብ ዒላማ አድርጎ ሲመታ ንጹሐን እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል።
በቀጣናው ያለውን ጂኦ-ስትራቴጂካዊ ፉክክር ተከትሎም ታሪካዊ ጸረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በውስጥ ተላላኪዎች በኩል የሚሸርቡትን የውክልና ሴራ በማክሸፍ ረገድ ሠራዊቱ የቆመበት ጽናት አኩሪ ነው።
ምርጥ ተዋጊ ማለት ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የሚያሸንፍ እና ስህተት የማይሠራ መሆኑን በማስመስከር፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በቀይ መለዮው ደምቆ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታጥቆ፣ የሀገር ኩራት እና የሰላም ዋስትና በመሆን የኢትዮጵያ ሕልውና የመጨረሻው እና የማይደፈረው ምሽግ ሆኖ ይዘልቃል።
የሠራዊቱ አባላት በየግንባሩ የሚያሳዩት የውጊያ ጥበብ እና የሞራል ልዕልና፣ ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ከጠላት እጅ ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል፣ አሁንም ወደፊትም ትውልድ የሚኮራበት ደማቅ ብሔራዊ ተቋም አድርጎታል።
በረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: