Search

ዓለም አቀፍ መርሕን የተከተለው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ

እሑድ ነሐሴ 10, 2018 51

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የምታራምደው ከውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ማጠንጠኛዎች አንዱ ዜጎችን ያስቀደመ እና የጋራ ተጠቀሚነትን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ነው።

ይህ አቅጣጫ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የንግድ አድማስን ለማስፋት የተነደፈ ስትራቴጂካዊ ምሰሶ ነው።

የዚህ ስትራቴጂ ዋነኛ ትኩረት የሆነው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ፣ የፖለቲካ ፍጆታ ሳይሆን 130 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ሕዝብ ግዙፍ የገበያ አቅም እና ከዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መርሆች አኳያ የማይታለፍ የሕልውና ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ወቅት የባሕር በር ማጣት በወጪ እና ገቢ ንግድ ላይ የሚያሳድረው የሎጂስቲክስ ወጪ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ፣ ይህን ስትራቴጂካዊ ጥገኝነት ማክተም ለማክሮ ኢኮኖሚው ጤንነት ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምታወጣው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በመቀነስ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ምርታማነት እና የግብርና ኤክስፖርትን ተወዳዳሪ ማድረግ አንኳር ግቧ ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከራስ ጥቅም ባሻገር ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰፊ የገበያ ትስስር የሚፈጥር ነው።

130 ሚሊዮን ሕዝብን የመግዛት እና የማምረት አቅም ከባሕር በር ጋር ማጣመር የቀጣናውን የኢኮኖሚ መዋቅር በማዘመን የጋራ ብልጽግናን ያረጋግጣል።

ይህ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በዓለም አቀፍ ሕግጋት እና በሰለጠነ የዲፕሎማሲ መርህ ላይ የተመሠረተ ነው።

ጥያቄው የሌሎችን ሉዓላዊነት የመጋፋት አዝማሚያ ሳይሆን፣ ... 1982 ወጥቶ 1994 ተግባራዊ በሆነው የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) የባሕር በር አልባ መንግሥታት ወደ ባሕር የመድረስ፣ በዓለም አቀፍ የውኃ አካላት ላይ የመንቀሳቀስ እና የባሕር ሀብትን በፍትሐዊነት የመጠቀም መብትን መነሻ ያደረገ ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረት ይህንን መብት በሁለትዮሽ ስምምነቶች እና በጋራ የልማት ሽርክናዎች አማካኝነት ተግባራዊ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።

የባሕር በር ለሚሰጡ አጋሮች የኢትዮጵያን የገበያ፣ የኃይል አቅርቦት እና የመሠረተ ልማት አቅም በጋራ የመጠቀም ዕድል የሚከፍት በመሆኑ ስምምነቶቹ ፍትሐዊ እና የተመጣጠነ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ናቸው።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ንቁ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና ከሕዝቧ አቅም የሚነሳው የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ሕጋዊነት ላይ የተመሠረተ እና የትውልድ ተሻጋሪ ብሔራዊ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ እርምጃ ነው።

በሃና ምንዳሁን

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: