Search

የብሔራዊነት ትርክት

ሰኞ ነሐሴ 11, 2018 88

በዓለማችን ላይ ያሉ ጠንካራ ሀገራት የተገነቡት በጸና ወታደራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ አቅም ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በሚያስተሳስርና በአንድ የጋራ ራዕይ በሚመራ ብሔራዊ ትርክት ጭምር ነው።

ትርክት ማለት ዓለምን፣ ሀገርን፣ አካባቢን እና ህዝብን የምንመለከትበት አጠቃላይ መነፅር ነው። ትርክት ዜጎችን በጋራ ዓላማ የሚያነቃቃ፣ የሀገር ፍቅርን የሚያሰርፅ እና ህዝብን ለጋራ ራዕይ የሚያሰልፍ ታላቅ ሀይል አለው።

የታላላቅ ሀገራትን ተሞክሮ ስንመለከት፣ የትኛውም ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ያለ አሰባሳቢ ትርክት ሊገነባ እንደማይችል እንረዳለን። ሀገራት የራሳቸውን ታሪክ፣ ስነ-ልቦና እና እሴት መሰረት ያደረገ ትርክት ገንብተዋል፡

አሜሪካውያን፡ "የአሜሪካ ልዩ መሆን" (American Exceptionalism) በሚለው እሳቤ እና በዴሞክራሲያዊ እሴቶቻቸው ላይ የተመሰረተ ትርክት በመገንባት፣ ዜጎቻቸው በሀገራቸው ታላቅነት እንዲኮሩና ዓለም አቀፍ ተፅእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ አድርገዋል። ይህንን ትርክታቸውንም በተለያዩ መንገዶች (እንደ ሆሊውድ ፊልሞች) ለትውልድ ያስተላልፋሉ።

 ጃፓናውያን፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስከፊ ውድመት በኋላ የሳሙራይ የጀግንነት ባህላቸውንና ለሀገር ክብር መስዋዕት የመሆን እሴትን፣ ከተፈጥሮ አክብሮትና ከዘመናዊ ስራ ወዳድነት ጋር በማዋሃድ፣ ሀገራቸውን ከአመድ ላይ አንስተው በዓለም የኢኮኖሚ ከፍታ ላይ አቆሙ።

ደቡብ አፍሪካውያን፡ ከአፓርታይድ አስከፊ የዘረኝነት እና የመከፋፈል ስርዓት ማግስት፣ "የቀስተ ደመና ሀገር" (Rainbow Nation) በሚል አቃፊ ትርክት፣ ልዩነታቸውን ወደ ውበት፣ አንድነት እና እርቅ ቀይረው ጠንካራ ሀገር መገንባት ቻሉ።

 ሲንጋፖር፡ ከትንሽ እና ደሃ ደሴትነት ተነስታ፣ አለም አቀፍ የፋይናንስ ማዕከል ወደ መሆን ያደረገችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ ትርክት የሀገረ መንግሥቷ ማንነት መቅረጫ አድርጋ ተጠቅማበታለች።

ወደ ሀገራችን ታሪክ ስንመጣ፣ ላለፉት ዘመናት ሲያጋጩን የነበሩት የተዛቡ ትርክቶች ወደ ጽንፍ ያዘነበሉ እና መካከለኛውን መንገድ የሳቱ ነበሩ። በዚህም የተነሳ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የመገንባት ጉዟችን ተስተጓጉሎ፣ በማይደፈሩ የሀገር ቀይ መስመሮች ላይ እንኳ ጠንካራ የጋራ ስምምነት እንዳይኖረን አድርጓል። ተቋማትም ይህንን በማስተካከል ፋንታ፣ የዚሁ ሰለባ ሆነው ቆይተዋል።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ይህንን ፈታኝ የአስተሳሰብ ጽንፍ ሰብሮ የሚወጣ፣ ህዝቦችን የሚያስታርቅ፣ አንድ የሚያደርግ እና ብዝሃነትን ከሀገራዊ አንድነት ጋር አዋህዶ የሚይዝ አዲስ ዕይታ ይፈልጋል። ይኸውም በመደመር እሳቤ ላይ የተመሰረተው የብሔራዊነት ትርክት ነው።

 የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ ሰርገኛ ጤፍ የተሰባጠረ ማንነት ያለው መሆኑን አምኖ በመቀበል፣ ሆኖም ግን ሀገራዊ አንድነትን እና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥትን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስቀድም መንገድ ነው።

ከቁዘማ ወደ ተስፋ መሻገር፡ ያለፈውን እያመነዠጉ ከመወቃቀስ ይልቅ፣ የትናንት ጥፋቶችንም ሆነ ድንቅ ልማቶችን የጋራ ታሪካችን አካል መሆናቸውን ተቀብሎ ዛሬንና ነገን በጋራ ብሩህ ለማድረግ ይሰራል፤ አዲሱን ትውልድም ከተስፋ መቁረጥ ይታደጋል።

እውነተኛ አካታችነት፡ ማንኛውንም ዜጋ በማንነቱ ሳያገል፣ ሁሉም በሀገሩ ግንባታ ላይ እኩል ድርሻና የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው በማድረግ ጥልቅ የወንድማማችነት እሴትን ያጎለብታል።

የሀገር ብሔራዊ ጥቅም፡ ከሀገር ህልውና፣ ሉዓላዊነት እና የጋራ ደህንነት የሚበልጥ አጀንዳ እንደሌለ በማስገንዘብ፣ ጠንካራ ብሔራዊ ስሜትን ይፈጥራል።

ይህ አሰባሳቢ እሳቤ ኢትዮጵያን ከተሰበረ እና ከተከፋፈለ የትናንት ታሪክ አውጥቶ፣ ወደማትናወጥ እና ፅኑ ሀገረ መንግሥትነት የሚቀይር ጉልበት አለው። ልዩነቶቻችንን በወንድማማችነት ማዕቀፍ ውስጥ በማስተናገድ ሀገራችንን ሁላችንም ወደምንመኛት ዘላቂ የብልፅግና ጎዳና የሚወስዳት ይኸው መንገድ ነው። ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ፈተና አሻግሮ ወደ ተፈጠረችበት ታላቅ የከፍታ ማማ የሚያወጣት፣ እንዲሁም የዜጎቿን ሰላምና ክብር በዘላቂነት የሚያረጋግጠው ጠንካራው የብሔራዊነት ትርክት ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: