Search

ጠመንጃዎች ታጥፈዋል፤ ጠረጴዛዎች ሞቀዋል!

ሰኞ ነሐሴ 11, 2018 104

በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ህንጻ መግቢያ በር ላይ፣ ለዓለም ሰላም እጅግ ጥልቅ የሆነ ትርጉም ያዘለ አንድ ግዙፍ የነሐስ ሐውልት ቆሞ ይገኛል።

ይህ ሐውልት "Non-Violence" (አመጽ አልባነት) ወይም በብዙዎች ዘንድ "The Knotted Gun" (የታጠፈው ጠመንጃ) በመባል ይታወቃል።

ስዊድናዊው አርቲስት ካርል ሮይተርስዋርድ እ.ኤ.አ. በ1980 የሠራው ይህ የታጠፈ ግዙፍ ሽጉጥ፣ ዓለም በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሰቃቂ እልቂት በኋላ፣ ከዚህ ወዲህ የፖለቲካም ሆነ የድንበር ቅራኔዎቿን በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የገባችውን ቃል ኪዳን የሚያስታውስ ሕያው መታሰቢያ ነው።

የሐውልቱ መልእክት እጅግ ግልጽ ነው፡- የጥፋት መሣሪያ የሆኑትን ጠመንጃዎችን እናጥፋቸው፣ በምትኩ ደግሞ የውይይት ጠረጴዛዎችን እናሙቅ!

ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ታላቅ የዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን እና መታሰቢያ በኋላ በእርግጥም ዓለም ጠመንጃዎቿን አጥፋ ሁሉንም ነገር በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ችላለች ወይ? ብለን ስንጠይቅ፣ መሬት ላይ ያለው እውነታ ፍጹም የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን።

አዎን፣ በርካታ የሰለጠኑ ሀገራት ዴሞክራሲን አዳብረው፣ የሐሳብ ልዩነቶቻቸውን በሰከነ ውይይት ለመፍታት እና ጠመንጃዎቻቸውን በሙዚየም ውስጥ ለማስቀመጥ ችለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ አሁንም ድረስ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ ለመፍታት የሚሞክሩ፣ ጠመንጃ ፈጽሞ ያልታጠፈባቸው በርካታ ሀገራት አሉ።

ከእነዚህ ሀገራት መካከል፣ በረዥም ታሪኳ የጦርነት እና የኃይል ፖለቲካ ሰለባ የሆነችው ኢትዮጵያ አንዷ ሆና ዘመናትን ተሻግራለች።

የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ኋላ መለስ ብለን በጥልቀት ስንቃኝ፣ በተለይም ከመካከለኛው ዘመን ወይም ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ታሪካችን ድረስ፣ ሀገራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮችን በኃይል የማስፈጸም እና በጉልበት የመፍታት አውዳሚ ባሕል ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደደ እና እየዳበረ መምጣቱን እንመለከታለን።

በዚያ ዘመን፣ የክልል ጌቶች እና የጦር አበጋዞች ልዩነቶቻቸውን በጦርነት ከመፍታት ውጭ፣ የሰላም እና የውይይት አማራጭን አይገነዘቡም ነበር።

ይህ በሆነበት አጋጣሚ፣ አውሮፓ እና የተቀረው ዓለም ወደ "የአብርሆት ዘመን" (Enlightenment Period) እየተሸጋገሩ ነበር።

የዘመነ ባርባሪዝም፣ የጭካኔ እና የጨለማ ዘመን አብቅቶ፣ የሐሳብ ገበታ እየሰፋ በሄደበት፣ ሳይንስ እና ፍልስፍና የሰዎችን አእምሮ በከፈተበት፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ የምክንያታዊነት ዘመን በፈነጠቀበት በዚያ ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ፣ ኢትዮጵያ ግን ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በጠመንጃ ከመመለስ አዙሪት ውስጥ መውጣት አልቻለችም።

በዚህ ችግሮችን በጠመንጃ ብቻ የመነጋገር አውዳሚ ባሕል ምክንያት፣ ሀገራችን ለዘመናት እጅግ ውድ ዋጋ ከፍላለች።

ስፍር ቁጥር የሌለው አምራች ትውልድ በጦርነት ሜዳ ተቀጥፏል፤ ልጆች አባቶቻቸውን፣ እናቶች ልጆቻቸውን በጠመንጃ አፈሙዝ ተነጥቀዋል።

ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሐሳብ ልዕልና ሳይሆን የጠመንጃ ፖለቲካ ሲሸጋገር፣ የኢትዮጵያ ምድር በገዛ ልጆቿ ደም ስትታጠብ ኖራለች።

ይህ የጉልበት እና የኃይል ፖለቲካ ዛሬም ድረስ ጠባሳው በሀገረ መንግሥት ግንባታችን ላይ በጉልህ ይታያል።

የፖለቲካ ልሂቃኑ ጠረጴዛ ዙሪያ ከመቀመጥ ይልቅ ጫካ መግባትን፣ በምክንያት ከመሞገት ይልቅ አፈሙዝ ማዞርን እንደ ብቸኛ አማራጭ ሲቆጥሩት ኖረዋል።

ዛሬ ግን፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚህ የጥፋት አዙሪት ለመውጣት እጅግ ወሳኝ በሆነ የታሪክ መታጠፊያ ላይ ቆማለች።

ከቅርብ ዓመታት የለውጥ ሒደት በኋላ እውን የሆነው "ሀገራዊ የምክክር ሒደት"፣ ዜጎች በየትኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በነፃነት እና ያለ አንዳች ፍርሃት እንዲወያዩ ሰፊ ዕድል የከፈተ ታላቅ ብሔራዊ ጅማሮ ነው።

ይህ ሒደት፣ በዋናነት ኢትዮጵያውያን የጠመንጃ አፈሙዝን አጥፈው፣ ሐሳብን በሐሳብ ወደሚሞግቱበት የሰለጠነ መድረክ የተሸጋገሩበት የመጀመሪያው ሕጋዊ እና ተቋማዊ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ሀገራዊ ምክክሩ፣ ኢትዮጵያ የነበሩባትን ውስብስብ ችግሮች ከሥረ መሠረታቸው አክሞ፣ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግ ታሪካዊ ፕሮጀክት ነው።

"ጠመንጃዎች መታጠፍ አለባቸው፤ መሞቅ ያለባቸውም የውይይት ጠረጴዛዎች ናቸው!" አሁን በኢትዮጵያ የምክክር አዳራሾች ውስጥ እውን እየሆነ ያለውም ይሄው ነው።

"የሚታኮሱ ሐሳቦች"፣ አጥፊ ጥይቶችን መተኮስ ትተው፣ ጠረጴዛን በጋለ ውይይት ማሞቅ ጀምረዋል።

ሰዎች በተፈጥሯቸው ምክንያታዊነትን የተላበሱ፣ ለመነጋገር እና ሐሳብን ለመለዋወጥ የተፈጠሩ ክቡር ፍጡራን ናቸው። የሰው ልጆች ሲለያዩ፣ ሲጋጩ እና የጥቅም መቃረን ሲያጋጥማቸው መፍትሔው መታኮስ አይደለም።

አፈሙዝ የጥፋት እንጂ የመፍትሔ ቋንቋ ሆኖ አያውቅም። በአንድ ጣራ ሥር ያደጉ፣ ከአንድ ማሕፀን የወጡ ወንድምና እህት እንኳ በሐሳብ ሊለያዩ ይችላሉ፤ ነገር ግን ልዩነታቸውን የሚያጠቡት በሰለጠነ ንግግር እና በመወያየት ነው።

ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በሐሳብ ፍጭት፣ በጥልቅ መደማመጥ እና በውይይት መፍታት የከፍተኛ ሥልጣኔ መገለጫ ነው። የሰው ልጅ ክብር የሚለካውም እርስ በርስ በመነጋገር፣ በመደማመጥ እና የሌላውን ሐሳብ በማክበር እንጂ፣ በመገዳደል አይደለም።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም፣ ይህንኑ ተፈጥሯዊ እና ሰብዓዊ የሥልጣኔ መንገድ የተከተለ፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት የማረቅ ብሔራዊ የፈውስ መድረክ ነው።

በመጨረሻም፣ ይህ ሀገራዊ ምክክር ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ባሕልን እንዲያዳብሩ፣ የሐሳብ ገበያቸውን እንዲያሰፉ እና ችግሮቻቸውን ወደ ፖለቲካዊ ጠረጴዛ አምጥተው እንዲፈቱ የተዘረጋ ታላቅ ድልድይ ነው።

ከጠረጴዛ ማለፍ የሌለባቸውን ሀገራዊ ቅራኔዎች፣ አሁን በጠረጴዛ ዙሪያ እየፈታናቸው ነው። ኢትዮጵያውያን ይህንን ታላቅ የውይይት እና የዕርቅ ምዕራፍ በተሳካ ሁኔታ የመሻገር፣ የነገዋን ኢትዮጵያም በጸና መሠረት ላይ የማቆም ሙሉ አቅሙም ሆነ ጥበቡ አላቸው።

እንደ ሐውልቱ መልእክት ጠመንጃን ለዘለዓለሙ አጥፈን፣ የፖለቲካ ጠረጴዛዎቻችንን በሞጋች እና ገንቢ ሐሳቦች አሙቀን፣ በጋራ አሸናፊነት የጸናች፣ የሰለጠነች እና ከፍ ያለች ኢትዮጵያን ዕውን እናደርጋለን!

 

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: