በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ያለውን ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ፤ ኮሚሽኑ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ በአዘጋጀው የአሰራር ሥርዓትና ዕቅድ መሠረት በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡
ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ጥልቅና ውስብስብ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልዩነቶች በምክክርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተከፈተ ታሪካዊ ዕድል ነው። ሂደቱ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ያለው ፋይዳ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ወገኖች በባለቤትነት ሊንከባከቡት ይገባል።
ኮሚሽኑ በሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ሂደቱን በነፃነት፣ በገለልተኝነት፣ በአካታችነት እና በአሳታፊነት ለማስኬድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። የምክክሩ ሂደት የማንኛውም ፓርቲ፣ የመንግሥት አካል ወይም የተለየ ቡድን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚውል መድረክ አይደለም፡፡ ይልቁኑም የተለያዩ ፍላጎቶችና አቋሞች በእኩልነት የሚቀርቡበትና በምክክር የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚሠራበት ሀገራዊ መድረክ ነው።
በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችም ነበሩ፡፡ በየመካከሉ በኮሚሽኑም ይሁን በተመካካሪዎች በኩል የተስተዋሉ ጉድለቶችና የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በአግባቡ ለመፍታትና ምላሽ ለመስጠት ጥረት በማድረግ ጭምር የተገኘ ውጤት ነው፡፡
ከዚሁ አኳያ የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴና ሂደቶችን በተመለከተ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅርቡ የሰጠውን መግለጫ አስመልክቶ የሚከተለውን ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በዚህ መሠረት ሂደቱ አካታችና አሳታፊ አይደለም የሚለውን የአብን አቋም ኮሚሽኑ ተገቢውን ምርመራና ማጣራት ካደረገ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲውን ድምዳሜ ኮሚሽኑ የማይጋራው መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡
በምክክር ጉባዔው ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከተቋማትና ማህበራት፣ የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የመንግሥት አካላት፣ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን፣ የቀድሞ ታጣቂ ኃይሎች፣ የዳያስፖራው ማህበረሰብ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወክለው የተለያዩ ድምፆች በሂደቱ እየተሳተፉና እየተደመጡም ይገኛሉ። አብንም እስካሁን በምክክር ሂደቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ኮሚሽኑ የማንኛውንም ተመካካሪ አቤቱታና ቅሬታ በቀላሉ የሚያልፈው ጉዳይ አይደለም።
አብንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በቅሬታ አፈታት ሥርዓቱ መሠረት ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። የምክክሩን ሂደት ለማሻሻል የሚቀርቡ ገንቢ አስተያየቶችና ቅሬታዎችም በተገቢው መንገድ በማየት የምክክር ሂደቱን ጤናማ እና ውጤታማ ለማድረግ እስከረዱ ድረስ በግብዓትነት ለመውሰድ ኮሚሽኑ ዝግጁ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዚሁ አጋጣሚ አብንንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በቀሪው የምክክር ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንዲተባበሩ ያክብሮት ጥሪውን ያቀርባል።
ሀገራዊ ምክክር የአንድ ወገን ድል ወይም የሌላ ወገን ሽንፈት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የምትሻገርባቸውን የጋራ መፍትሔዎች ለማፈላለግ የሚያግዝ፤ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ ሂደት ነው። ኮሚሽኑም የሁሉንም ዜጎችና ተመካካሪዎች ድምፅ በእኩልነት ለማዳመጥና ሂደቱን በነፃነትና በገለልተኝነት ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት ዳግም ያረጋግጣል።
በመጨረሻም ኮሚሽኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና ልዩ ልዩ ተቋማት ለምክክሩ ስኬታማነትና የሚያደርጉትን ቀጣይነት ያለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አጥብቆ ያሳስባል።
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው!
ሀገራዊ ምክክር፤ ለሀገራዊ መግባባት!
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ነሐሴ 11 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: