Search

በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር በነበረው የድብደባ ቪዲዮ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ፖሊስ ገለጸ

ሰኞ ነሐሴ 11, 2018 136

በማህበራዊ ሚዲያ አንዲት ታዳጊ ስትደበደብ የሚያሳይ ቪዲዮን በተመለከተ ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራ ማጣራቱን አስታውቋል፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አለም ባንክ አካባቢ አንዲት ታዳጊ ስትደበደብ የሚያሳይ አሳዛኝ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉትን ተጠርጣሪዎች በህግ እንዲጠየቁ ህብረተሰቡ አስተያየት እየሰጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ድርጊቱ ጥቅምት 14 ቀን 2018 መፈፀሙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቆ፤ ቪዲዮው በማህበራዊ ሚዲያ ከመሰራጨቱ ከወራት በፊት ወንጀሉን ፈፅመዋል የተባሉትን ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ማጣራቱን ፖሊስ ገልጿል፡፡ 

በወንጀሉ የተጠረጠሩት ሦስት ተማሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው በጊዜ ቀጠሮ ታስረው ፖሊስ አስፈላጊውን ማስረጃ በማሰባሰብ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ መዝገቡን ለሚመለከተው የፍትህ አካል መላኩን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ 

ልጅቷ ስትደበደብ የሚያሳየው ቪዲዩ መለቀቁ በልጅቷም ሆነ በቤተሰቧ ላይ አሉታዊ  ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ቪዲዮውን የለቀቀውን አካል ለማረጋገጥ ፖሊስ ሦስቱን ተጠርጣሪዎች በድጋሚ በቁጥጥር ስር አውሎ ተጨማሪ  ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡

 

ህብረተሰቡ ድርጊቱን በማውገዝ ወንጀሉን ፈፅመዋል የተባሉትን ተጠርጣሪዎች በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ያሳየውን መቆርቆር የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አድንቋል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: