Search

ከዕለታዊ ጫና ወደ ተፈጥሮ እቅፍ፡- የአረንጓዴ አሻራና የኮሪደር ልማት ለአእምሮ እፎይታና ለከተሞች አዲስ ህይወት

ሰኞ ነሐሴ 11, 2018 69

ሕይወት በውጥረትና በተደጋጋሚ እንቅስቃሴ በምትሞላበት በዚህ ዘመን፣ አእምሮ ከዕለት ተዕለት ጫና ራሱን ለማሳረፍና ሰላምን ለማግኘት ተፈጥሯዊ መጠለያዎችን ይፈልጋል።

የአረንጓዴ አሻራ የጋራ ጥረት ውጤት የሆኑ ለምለም ስፍራዎች አካባቢን ከማስዋብ ባለፈ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያርፉ፣ እንዲወያዩና ከዕለታዊ ጫና ለጥቂት ጊዜ እንዲርቁ አዲስ የመንፈስ እፎይታና የአእምሮ እረፍት ይሰጣሉ።

በአረንጓዴ እፅዋት ከተከበቡ መናፈሻዎች የሚገኘው ተፈጥሯዊ ጸጥታ፣ የአእዋፍ ድምፅና የአበቦች መዓዛ አእምሮን ከተወጠረበት ሁኔታ ቀስ ብሎ ወደ መረጋጋት እንዲመለስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከተፈጥሮ ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ ችግኞችን መትከል፣ ማጠጣት፣ አረም ማረምና መንከባከብ በጭንቀትና በውጥረት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አላቸው።

እነዚህ ትኩረትን የሚጠይቁ ተግባራት ሰውን ከዕለታዊ ሀሳቦች አርቀው በሚያደርገው የበጎ ስራ ላይ እንዲያተኩር ከማድረጋቸውም በላይ፣ ከቀላል እስከ መካከለኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ከማስገኘታቸው ጋር ተያይዞ የአንድን ተክል እድገት ከትንሽ ችግኝነት እስከ ለምለምነት ማየት የስኬትና የዓላማ ስሜትን ያጠናክራል።

ይህም ከተፈጥሮ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር ለሰውነት እንቅስቃሴና ለስሜት መረጋጋት ትልቅ ድርሻ አለው።

ይህንን የተፈጥሮ እፎይታ በከተሞች ውስጥ ለማስፋፋት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትም በከተማዋ መሃል የሚገኙ አረንጓዴ ስፍራዎችን፣ የእግረኛ መንገዶችን፣ መናፈሻዎችንና የመዝናኛ ቦታዎችን ከዘመናዊ የከተማ ልማት ጋር በማዋሃድ የነዋሪዎች ማረፊያና መገናኛ እያደረጋቸው ይገኛል።

የአረንጓዴ አሻራና የኮሪደር ልማት ተፈጥሮን የመጠበቅና ከሰው ልጅ ዕለታዊ ኑሮ ጋር የማገናኘት ታላቅ ሀገራዊ ርዕይ በመሆናቸው፣ ዛሬ የተተከለው ዛፍ የነገ ጥላ፣ ዛሬ ያለማነው አረንጓዴ ስፍራ ደግሞ ነገ ሰዎች የሚገናኙበት፣ የሚያስቡበትና እፎይታ የሚያገኙበት ዘላቂ ሀብት ሆኖ የሚያገለግል ነው።

 

በልዩ እሸቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: