በሀገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት የተከማቹና ሲንከባለሉ የመጡ ውስብስብ የፖለቲካ ጥያቄዎችን በሰላማዊ ውይይት በመፍታት ረገድ ታሪካዊ ምዕራፍ እየተጻፈ ይገኛል።
ታሪካዊ ስብራቶችን በመጠገን የተሻለች ሀገር ለወደፊት ትውልድ የማሸጋገር ታላቅ ርዕይ የሰነቀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ሺህ ተሳታፊዎችን በአዲስ አበባ አቅፎ የጀመረውን ታላቅ ሀገራዊ ጉባኤ አሁን ላይ አንድ ወር አስቆጥሯል።
ይህ ሂደት ያለፈውን ችግር አድበስብሶ ከመሸፈን ይልቅ፣ ሀገርን ባስቀደመ ወንድማማችነታዊ መንፈስ እውነትን በመጋፈጥ የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች በጥልቀት ለመረዳትና ዘላቂ መፍትሔዎችን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለማመንጨት ያስቻለ ቁልፍ ሂደት ሆኖ ወደ ወሳኙ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
ኮሚሽኑ ባለፈው አንድ ወር ያካሄደውን ጉዞ ሲገመግም፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከር ባሳዩት ቁርጠኝነትና እርስ በእርስ ባዳመጡበት ጥልቅ አክብሮት "የአንተ ችግር የእኔ ነው" የሚል የመደጋገፍ ባህልን አጎልብተዋል።
በተለይም የምክክር ጉባኤው ተመካካሪዎችን ፊት ለፊት ከማገናኘታቸው በፊት ስሜታቸውን በማረገብና በይቅርታ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር ሰላምን ከሚመልሱት የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጥበብ ትልቅ ልምድ የተቀዳ በመሆኑ፣ እውነተኛ ሰላም የሚረጋገጠው የሌሎችንም ሕመም መታመም ስንጀምር መሆኑ ተመላክቷል።
በመሆኑም ተመካካሪዎችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፅንፈኛ የራስ ፍላጎትና ከቆዩ አጉል ልማዶች በመላቀቅ በሌሎች ጫማ ላይ ቆሞ ስጋታቸውን በመጋራት የእርስ በእርስ መተማመንን መገንባት ይኖርባቸዋል።
ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም እና የሥራ እድል ፈጠራ ያለ ተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሊፀኑ የማይችሉ በመሆናቸው፣ ይህ ሀገራዊ ምክክር የግጭት መንስኤዎችን በማከም የተረጋጋ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመትከል፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባትና ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር መሠረት በመጣል ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ልማት አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚከፍት ወሳኝ ሂደት ነው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: