Search

መንግስት የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል ወሰነ

ማክሰኞ ነሐሴ 13, 2017 150

የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ መመሪያ ኃላፊ አቶ ሙላይ ወልዱ ለኢቢሲ እንደገለጹት፤ የገንዘብ ሚኒስቴር በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ማሻሻያ መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡

ነባሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከምጣኔ ውጭ ሌሎች ማሻሻያዎችን በማካተት 3 አስርት ዓመታት በኋላ ተሻሽሎ 2017 በጀት አመት ስራ ላይ መዋሉን አቶ ሙላይ ገልፀዋል፡፡

የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከነበረው 12 በመቶ በላይ ድርሻ በየዓመቱ በተከታታይ እየቀነሰ 7 በመቶ በታች መድረሱን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ከዚህ ጠቅላላ ቅናሽ 44 በመቶው የተጨማሪ እሴት ታክስ ድርሻ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስ ህጉን አሁን ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ የቀጣይ ዓመታት ለውጦች ጋር እንዲጣጣም በማድረግ በመካከለኛ ዘመን የገቢ ስትራቴጂው መሰረት ተሻሽሎ 2017 በጀት ዓመት ስራ ላይ እንዲውል መደረጉንም አውስተዋል፡፡

መጣኔው አሁን ካለበት 15 በመቶ ከፍ እንዲል ማድረግ ጫናው ተጨማሪ እሴት ታክስ በአግባቡ የሚከፍሉት ላይ እንዲባባስ በማድረግ የታክስ አስተዳደር ወይም የታክስ ህግ ተገዥነት ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በማሻሻያው መሰረት በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ማሻሻያ መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ ምጣኔ 15 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል መወሰኑን ነው የገለፁት፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስ ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች ውስጥ የሚመደብ ሆኖ በፍጆታ የሚጣል፣ ቁጠባንና ካፒታልን የሚያበረታታ ከተጠቃሚው የሚሰበሰብ ታክስ ነው፡፡

በጌታቸው ባልቻ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #tax