በዚህ ዓመት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሀገር ውስጥ በተመረቱ ተተኪ ምርቶች ከ 4.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጥላሁን ዓባይ ገለፁ።
በኢቢሲ አዲስ ቀን የዜና መሰናዶ ላይ እንግዳ የነበሩት አቶ ጥላሁን፤ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚመረቱ ተኪ ምርቶች አመርቂ ውጤት እያስገኙ ነው ብለዋል፡፡
ባለሀብቶች እንዲበረታቱ መሠረት የመጣል እና አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማስፋት ስራ እየተሰራ እንደሆነም ገልፀዋል።
በየአመቱ አዲስ የሚቋቋሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ቁጥራቸው 1 ሺህ 100 ሲሆን ከለውጡ በኋላ ከ4 ሺህ 285 በላይ አዳዲስ የአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማብቃት መቻሉን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።
ለኢንዱስትሪው ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን፣ የመሬት እና የመስሪያ ቦታ ዝግጅቶችን እንዲሁም ከፋይናንስ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ድጋፍ ከመስጠት አኳያ በተለይም የክህሎት ግንባታን በማደራጀት ረገድ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሀገር ደረጃ ኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ 96 የስትራቴጂክ ተኪ ምርቶች ተለይተው በአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ የተመረቱ ሲሆን፤ በዚህም ከ832 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ ውጤት አነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሀገርን የኢንቨስትመንት መሰረት ከማስፋት በዘለለ ተተኪ ምርቶች ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ማሳያ መሆኑንም አቶ ጥላሁን ገልፀዋል።
በሔለን ተስፋዬ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #industries