በህይወት ዘመን ቆይታቸው ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ተመራማሪ፣ ደራሲ ብሎም አምባሳደር መሆን የቻሉ ናቸው።
ከአባታቸው ቀኝ አዝማች ረታ ወልደአረጋይ፣ ከእናታቸው እማሆይ አፀደ ረድኤቱ ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም ነበር በአዲስ አበባ የተወለዱት።
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በዘመኑ በነበረው ማህበረሰባዊ ልማድ መሠረት የአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርታቸውን ተማሩ።
በ1934 ዓ.ም የ7 ዓመት ዕድሜ ሲሞላቸው በቀድሞ መጠሪያው ደጅ አዝማች ገብረማሪያም፡ በኋላም ሊሴ ገብረማሪያም በሚል ስያሜ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፈረንሳይ ትምህርት ቤትን ተቀላቀሉ።
የ2ኛ ደረጃ ተማሪ እያሉም የስነ ፅሁፍ ችሎታቸው 'እኔ እና ክፋቴ፣ የገዛ ስራዬ፣ ፍቅር ክፋ ችግር እና እንግዳ ሰው የቡልጋው' በሚል ርዕስ በራሳቸው ተፅፎ የተዘጋጀውን ቴአትር ለተመልካች እንዲያቀርቡ አስችሏቸዋል።
ከነዚህ መካከል 'እኔ እና ክፋቴ' የተሰኘው ስራ በብዙዎች ዘንድ የተወደደ እና እውቅናንም ያስገኘላቸው ነበር።
የምናብ እይታቸው እና ነገሮችን የሚያጤኑበት መንገድ በወቅቱ በነበሩ አመራሮች አይን ያስገባቸው አምባሳደር ዘውዴ ገና የ18 ዓመት ወጣት ሳሉ ነበር የጋዜጣ እና የማስታወቂያ መስሪያ ቤት በመባል ይጠራ የነበረው የመንግስት ተቋምን በጋዜጠኝነት ለማገልገል የተቀላቀሉት።
ከዕድሜያቸው የሚልቀው ታታሪነት እና ለሞያ መሰጠትም በገነተ ልዑል ቤተመንግስት (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) የመጀመሪያው ዜና መዋዕል ዘጋቢ ሆነው እንዲመደቡ አስቻለ።
ይህ ደግሞ ከንጉሱ ጋር እንዲተዋወቁ በቤተመንግስቱ ያለውን መስተጋብር እንዲገነዘቡ ያስቻለ ክስተት ነበር።
የሀገሪቱ የውስጥም ሆነ የውጪ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴን ከውስጥ ለመከታተልም እድሉን አመቻቸላቸው።
ይህን እያደረጉ በኢትዮጵያ ራዲዮ ዜና አቅራቢ በመሆን ለ3 ዓመታት ማገልገላቸውም ታሪካቸው ያስረዳል።
በዚህ ሁኔታ ላይ ችሎታቸውን ያስተዋሉት ንጉሱም ወደ ውጭ አቅንተው እንዲማሩ የትምህርተ እድል አመቻቹላቸው።
ከ1948 እስከ 1952 በፈረንሳይ፧ ፓሪስ የጋዜጠኝነት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ቆዩ።
ከትምህርት ቆይታ ሲመለሱም በለጋ እድሜ የጀመረው ሀገርን ማገልገል በላቀ እውቀት ተደግፎ ቀጠለ።
ከ1952 እስከ 1954 የኢትዮጵያ ድምፅ መነን መፅሔት ዋና ዳይሬክተር እና የአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅ በመሆንም ሰሩ።
እንዲሁም በ1954 የኢትዮጵያ ራዲዮ የብሔራዊ ፕሮግራም ዳይሬክተር ለመሆን በቅተዋል።
ይህ ከበርካታ ሚኒስትሮች እና የስራ ኃላፊዎች ጋር ሲያገናኝ እና የአካሄድ ሂደትን እያስቃኘ ያመጣቸው ጉዞ በ1962 የዲፕሎማሲ መንገድ ላይ አድርሷቸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እና በጣሊያን እና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ መልዕክተኛ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ህዝባቸውን እና ሀገራቸውን አገልግለዋል።
በተለያዩ መንገዶችም እውቀት እና ልምዳቸውን በማካፈል እውቅና መቀበል የቻሉ እንቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
አምባሳደር ዘውዴ ለስራ ጉዳይ ወደ ለንደን ከተማ አቅንተው በነበረ ወቅት ባጋጠማቸው ድንገተኛ የጤና እክል በህክምና ሲረዱ ቆተው መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
በአፎምያ ክበበው