በጎንደር ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውና ለረጅም ዓመታት በግንባታ ሂደት ውስጥ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ተተብትበውበት የቆየው የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት፣ አሁን ላይ ከነበረበት ተስፋ የመቁረጥ ምዕራፍ ወጥቶ ወደ መጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ለዓመታት የነዋሪዎች የቅሬታና የጥያቄ ምንጭ ሆኖ የቆየው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በተወሰደ ቁርጠኛ ውሳኔ ተቋራጩ እንዲቀየር ከተደረገ በኋላ እንደ አዲስ ነፍስ ሊዘራበት ችሏል።
መሠረታዊ ችግሮቹ ከተቀረፉ በኋላ ግንባታው ሌሊትና ቀን ለ24 ሰዓታት በተቀናጀ ሁኔታ በመከናወኑ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 94 በመቶ ማድረስ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት 32 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩቢክ ሜትር የውሃ ይዘትና 34 ሜትር ጥልቀት ያለው ይህ ግድብ፣ ቀሪ ሥራዎቹ በክረምቱ ዝናብ መውጣት በጥቂት ወራት ውስጥ ተጠናቀው ሙሉ በሙሉ ለአገልግሎት እንደሚበቁ ይጠበቃል።
የመገጭ የመስኖ ግድብ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት ግዙፍ አቅም ያለው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በመጀመሪያው ዙር ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የሚያስችል የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ ይገኛል።
ይህ ፕሮጀክት የአካባቢውን የግብርና ምርታማነት ከማሳደጉ ባሻገር ለጎንደር ከተማና ለአካባቢው ማህበረሰብ አስተማማኝና ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋል።
ለዓመታት የሕዝብ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የመገጭ ግድብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳየው ፈጣን አፈጻጸም፣ በአገራችን እየተገነቡ ያሉ የመስኖና የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት የማጠናቀቅ አዲስ የሥራ ባህል እየጎለበተ መምጣቱን በተግባር ያሳየ አበረታች ማረጋገጫ ነው።
በሙሉ ግርማይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: