Search

እስከ 1 ሚሊዮን ብር የሚያስቀጣው የኃይል ስርቆት

Aug 19, 2025

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ከኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ወቅታዊ ዝግጅት ጋር በተቋሙ የአሠራር ማሻሻያ፤ የደንበኞች አገልግሎት እና የኃይል መቆራረጥ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።

የአገልግሎቱ የፕሮሰስና ኳሊቲ ማኔጅመንት ሥራ አስፈጻሚ አቶ እሱባለው ጤናው  በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥  ባልተገቡ ተግባራት ምክንያት የኃይል ብክነት እያጋጠመ ነው።

የዚህ ምክንያቱ ዝቅተኛ ክፍያ እንዲቆጥር በማለት ከቆጣሪ ላይ በአንዳንድ ደንበኞች በሚፈጸም የኃይል ስርቆት እንደሆነ ገልጸዋል።

ድርጊቱ ወንጀል በመሆኑ በተለያየ እርከን አዲስ የቅጣት ምጣኔ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በመኖሪያ ቤት 20 ሺህ ብር፤ በንግድ ቤት 500 ሺህ ብር በኢንዱስትሪዎች ላይ ደግሞ ከ750 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር ድረስ መቀጮ እንደሚኖር አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል ተቋሙ የሚያስከፍለው የአገልግሎት ታሪፍ ጥገናን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ፤ ደንበኞች ለጥገና ተሰማርተው ጉቦ ለሚጠይቁ የአገልግሎቱ ባለሙያዎች ሕገ-ወጥ ተግባር ከመተባበር ይልቅ ጥቆማ እንዲሰጡ የማርኬቲንግ ሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ደንድር ጠይቀዋል።

የአገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ገበየሁ ሊኪሳ በበኩላቸው፥ ተቋሙ በ2030 በመላው ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ደንበኞች ለሚያነሷቸው ቅሬታዎች ትርጉም ባለው መልኩ መፍትሔ ለመስጠት መሰረተ ልማትን ማዘመን ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት 800 ሺህ ተጨማሪ ደንበኞችን ለማፍራት መታቀዱንም አንስተዋል።

ከተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ጋር በተያያዘ ደንበኞች ያነሱት ቅሬታ ተገቢ መሆኑ የታመነበት ሲሆን፤ በአፈጻጸም ክፍተት ምክንያት ለተፈጠረው ችግር አገልግሎቱ ይቅርታ ጠይቋል።

በቤተልሔም ገረመው

#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #ኢኤኃ #የኃይልስርቆት