የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነትና የሀገር ልዕልና በጥብቅ የተመሠረተው በጽኑ ውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ ላይ በተገነባ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ነው።
ጠንካራ ሀገርን መገንባት የሚቻለው ውስጣዊ ስንጥቆችን በበሰለ አካሄድ ጠግኖ በአብሮነት በመቆም በመሆኑ፣ ይህ ተግባር ለነገ የሚባል የማይታለፍ አገራዊ የቤት ሥራ ነው።
በተለያዩ የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ የቀየሰችው የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ የጎረቤት ሀገራትን ትብብር፣ የኢኮኖሚ ትስስርና ብሔራዊ ጥቅምን በማዕከል ያደረገ ሲሆን፣ ይህም የውጭ ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት በከፍተኛ ደረጃ አጠናክሮታል።
በአዲሱ የፖሊሲ ማዕቀፍ ዲፕሎማሲ ከጥቃት መከላከያ ማሻገርያነት ባለፈ፣ ለልማትና ለብልጽግና አዲስ መንገድ የሚከፍት ቁልፍ መሣሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
ለዚህም ዋነኛው ሀገራዊ ማሳያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲሆን፣ ግድቡ የኢትዮጵያን የኃይል ፍላጎት ከመሙላት ባሻገር የቀጠናውን የኃይል ትስስርና የጋራ የልማት ዕድል የሚያሰፋ ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ሆኗል።
በተመሳሳይ መልኩ የባሕር በር ጉዳይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ከቀጣናዊ ትስስርና ከኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ጋር ተያይዞ በሰላማዊ መንገድና በውይይት የሚቀጥል ሲሆን፣ ይህም የሰላም አማራጮችን በማስቀደም የጋራ ዕድገትን እውን ለማድረግ የሚደረግ የማይናወጥ ጽናት ማሳያ ነው።
የዚህ ውጤታማ ዲፕሎማሲ ሌላው ዋነኛ ማዕከል ዜጋ ተኮር አሰራር ነው።
በውጭ ሀገራት በስደትና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎችን በክብር ወደ ሀገር መመለስ፣ ሕጋዊና የሰብዓዊ ክብርን የጠበቀ የውጭ ሥራ ስምሪት ሥርዓት መዘርጋት፣ እንዲሁም ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር ያለውን ትስስር ማጠናከር በከፍተኛ ትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የውጭ ተሰሚነት እውነተኛ መሠረት የውስጥ አንድነት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ በመሆኑ፣ አገራዊ የውስጥ አቅም በጠነከረ ቁጥር ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ይከበራል፤ በዓለም አቀፍ መድረክም ጠንካራና ተሰሚነት ያለው ድምፅ ማሰማት ይቻላል።
በስምረት ገዛኸኝ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: