Search

ለህዳሴ ግንባታ ዓለም አቀፍ ድጋፍ የተነፈግንበት ከባዱ ወቅት ልክ እንደ ክረምቱ አልፏል!

Aug 19, 2025

በሰኔ 26 ቀን የሚገባው የክረምት ወቅት በወርሃ ሐምሌ እና በነሐሴ የመጀመሪያ ቀናት በከፍተኛ የዝናብ መጠን መሬቱን ያርሳል።

ሆኖም በነሐሴ ወር አጋማሽ ምድሪቱ እየፀናች፤ ከፍተኛ የዝናብ መጠን እየቀለለ እንደሚሄድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተማሪ የሆኑት መምህር አብነት ይገልፃሉ።

"ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት" እንደሚባለው ከደብር ታቦር ክብረ በዓል በኋላ ያለው የክረምት ዝናብ እየተመጠነ፤ የመጸው የብርሃን ወቅት እየቀረበ ነው ብሎ ሀገሬው እንደሚያምን ይናገራሉ።

የክረምቱ ወቅት ሲያልፍ የተዘሩ አዝርዕት ከአፈር ጋር ተዋህደው ማቆጥቆጥ የሚጀምሩበት ነው ሲሉም መምህር አብነት ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልፀዋል።

አሁን ከባዱን ክረምት በራሷ አቅም ያለፈችው ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ዓለም አቀፍ ድጋፍ የተነፈገችበትን ከባድ ወቅትም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አልፋዋለች የሚሉት ደግሞ ጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር፣ ኢ/ር) ናቸው።

ቀድሞ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የነበሩት ዶ/ር ጥላሁን አሁን የአፍሪካ ቀንድ እና መካከለኛው ምሥራቅ ጂኦፖለቲካ ተመራማሪ ናቸው።

ታላቁን የዓባይ ወንዝ ለመገደብ ስናስብ ያለፍንባቸው ጫናዎች፣ በተከታይም ለፋይናንስ ድጋፍ ስናመራ ዝግ ሆነው የጠበቁን በሮች ቢኖሩም ያ ወቅት አልፎ የብርሃን ዘመን ልናይ ነው ሲሉ በተለይም ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።

ከ60 በመቶ በላይ ዜጎቻችን በጨለማ የኖሩበት፣ ግብርናችን በሚገባው ልክ ያላደገበት፣ ከተጠቃሚነት የስምምነት መድረክ የተገለልንበት ሁኔታ አብቅቷል ሲሉ ገልፀዋል።

በቀጣይ ለሚመጡ ግድቡን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ዲፕሎማሲያዊ የቤት ሥራዎች ራስን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በመጪው የመጸው ወቅት ያመነጨነውን ብርሃን መጠቀም እና መጠበቅ መቻል ላይ ልናተኩር ይገባል በማለትም አፅንዖት ሰጥተዋል።

በአፎሚያ ክበበው

#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #ክረምት #መጸው