Search

ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች

Aug 19, 2025

በ2017 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ 4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሏን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

ይህ አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ2.2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አራጌ ክብረት ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልፀዋል።

ከዚህም ባለፈ ውጤቱ ባለሀብቶች በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ያላቸውን እምነትን የሚያሳይ ነው ብለዋል አቶ አራጌ።

በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ለ525 አዳዲስ እንዲሁም ለ19 የማስፋፊያ ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ መሰጠቱንም ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።

የወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፉ ለውጭ ባለሃብቶች መከፈቱን ተከትሎ ለ61 ኩባንያዎች አዲስ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ይህም በዘርፉ ስላለው ዓለም አቀፍ ፍላጎት ማሳያ ነው ብለዋል።

ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በማጣጣም 14 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን (10 በመንግሥት እና 4 በግል ባለቤትነት የተያዙ) ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ማሸጋገር እንደተቻለም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት መቻሏንም ነው የጠቆሙት።

በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ሥራዎች መካከል ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም መዘጋጀቱ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በፎረሙ ከ42 ሀገራት የተውጣጡ ከ700 በላይ ባለሃብቶችን ተሳታፊ በማድረግ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማግኘት ተችሏል ብለዋል።

የኮሚሽኑን አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ዲጂታይዝ በማድረግ ባለሀብቶች ሁሉንም የምዝገባ፣ የፈቃድ አሰጣጥ እና የድህረ ኢንቨስትመንት ድጋፎች በኦንላይን እንዲያገኙ ማድረግ እንደተቻለም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተገማች እና ለኢንቨስተሮች ተስማሚ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠር በማሰብ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ 3 ዋና ዋና የሕግ ማሻሻያዎች እንዲፀድቁ ማድረጉን አንስተዋል።

በሰለሞን ከበደ

#EBCdotstream #ETV #EIC #FDI