አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን ሀገር ወዳድነትን አስርፆ ያለፈ ታላቅ የሙያ አባት ነው ሲሉ የሙያ አጋሮቹ ገለጹ።
የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሙያ አጋሮቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈጽሟል።
የጥበብ አጋሩ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ፤ አርቲስት ደበበ እሸቱ ከሙያ አጋሩ ወጋየሁ ንጋቱ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የኪነ-ጥበብ ታሪክ በወሳኝ ምዕራፍ ማሸጋገር የቻለ አንጋፋ የጥበብ ሰው ነበር ብሏል።
ከኪነ-ጥበብ ሥራዎቹ ባለፈም ለብዙዎች በአርዓያነት የሚወሰድ የመልካም ስብዕና መገለጫ የሆነ ደግና በሥራ ትጋት የተገነባ ጠንካራ ሰው እንደነበር ገልጿል።
ሌላኛው የሙያ አጋሩ አርቲስት ደበሽ ተመስገን፤ ጋሽ ደቤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የኪነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ቀዳሚና ጉምቱ ከሚባሉ የጥበብ አባቶች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነበር ብሏል።
በኪነ-ጥበብ ሥራውም ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በአህጉረ አፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የገዘፈ ስምና ዝናን ያተረፈ ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ታላቅ አባት እንደነበርም ገልጿል።
አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ፤ አርቲስት ደበበ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በትልልቅ መድረኮች የምንሰራበትን ዕድል በማመቻቸት ትልቅ የሙያ አባታችን ነበር ብላለች።
በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃም ዘመን ተሻጋሪ ታላላቅ ሥራዎች ሰርቶ ያለፈ የጥበብ አውራ እንደነበር ገልፃለች።
አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ አርቲስት ደበበ እሸቱ ከኪነጥበብ ሙያ ባለፈ ሰው አክባሪነት፣ ቅንነትና ታታሪነትን አስተምሮ ያለፈ በርካታ ጸጋዎችን የታደለ አባት እንደነበር ገልጿል።
የአንጋፋው የጥበብ ሰው የሥራ ውጤቶችም ኢትዮጵዊነትን በማቀንቀን፣ ሀገር ወዳድነትን በማስረጽ የተገነባበትን ስብዕና በግልጽ የሚያሳዩ መሆናቸውን መናገሩን ኢዜአ ዘግቧል።
አርቲስት ሰለሞን ታሼ (ጋጋ)፤ የአርቲስት ደበበ እሸቱ ሥራዎች ከሀገር ውስጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የናኙ መሆናቸውን ገልጿል።
አንጋፋው አርቲስት በሕይወት ዘመኑ ለሀገሩና ለወገኑ ካበረከታቸው ዘርፈ ብዙ የኪነ-ጥብብና ሌሎች ሥራዎች በተጨማሪም ከሥልፈቱ በኋላም የዐይን ብሌኑን ለግሶ ያለፈ የሀገር ባለውለታ መሆኑን ተናግሯል።
ሁለገቡ የጥበብ ሰው በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን በማገልገል ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ በሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት አበርክቶለታል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅም "ኢትዮጵያን ስላገለገሉ ኢትዮጵያ ታመሠግናለች" በሚል መሪ ሃሳብ በተሰናዳው ሀገራዊ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የክብር ሜዳይ ተቀብሏል።
በአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የሙያ አጋሮቹ እና ወዳጅ ዘመዶቹ ተገኝተዋል።
#EBCdotstream #DebebeEshetu #Funeral #fmrcolleagues