Search

"ረጅም ጊዜ የፈጀው የጽምዶ ጥምረት በጥቂት ጊዜ ፈርሷል"፡- አቶ ጌታቸው ረዳ

ሓሙስ ጥቅምት 12, 2019 121

ረጅም ጊዜ የፈጀው የጽምዶ ጥምረት በጥቂት ጊዜ መፍረሱን እና የኢትዮጵያን መበታተን የሚመኙ የውጭ ኃይሎች ስሌትም መክሸፉን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

ሚኒስትሩ በሰጡት ሰፊ የጂኦፖለቲካዊ ትንታኔ፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ለበርካታ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች የሚያጋልጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መልክዓምድር በቀላሉ የማይቀየር ወይም ለውጥን የሚገታ በመሆኑ፣ ሀገራት የሚኖሩበት አካባቢ የሰላም፣ የፖለቲካ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ እድገት ፈተናዎቻቸውን እንደሚወስነው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃ ዋና ምንጭ እና የታሪካዊ እምነቶችና ባህሎች መገናኛ ድልድይ ብትሆንም፣ በተለይ እንደ ግብፅ ያሉ ሀገራት የኢትዮጵያ መረጋጋት ለደህንነታቸው ስጋት እንደሆነ በማመን የውስጥ ድክመቶችን ሲቦረቡሩ መኖራቸውን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል።

ግብፅ ሳይንስን እና ታሪክን በማዛባት፣ በየጊዜው የሚነሱ የውስጥ ተቃዋሚዎችን እና ፀረ-መንግሥት እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ የኢትዮጵያን እድገት ለማደናቀፍ ስትሰራ መቆየቷንም አክለዋል።

በቅርቡ የተዋቀረውን የሕገወጡ ህወሓት፣ ራሱን ፋኖ  ብሎ የሚጠራው ቡድን እና የሌሎች ስብስቦችን ጥምረት አስመልክተው አቶ ጌታቸው ሲናገሩ፣ "ጽምዶ" የሚለው ቃልና ጽንሰ-ሐሳብ ራሱ ከሻዕቢያ (ህግደፍ) የጽሑፍ ሰነዶች የተቀዳ እና የተጫነ መሆኑን ገልጸዋል።

ሻዕቢያ የራሱን ስትራቴጂካዊ የድንበር ስጋት ለማራቅ እና ኢትዮጵያን በማተራመስ ህልውናውን ለማስቀጠል ያቀደው ይህ ጥምረት፣ በውስጣዊ የፖለቲካ ቅራኔ የተሞላ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና የህዝብ ድጋፍ የሌለው እንደነበር አብራርተዋል።

እንዲሁም በመከላከያ ሠራዊቱ ፈጣንና ቀልጣፋ ምላሽ ምክንያት ለመመስረት የወሰደበትን ያህል ጊዜ እንኳ ሳይወስድ ሙሉ በሙሉ መፍረሱን እና መክሸፉን አስታውቀዋል።

"ከጠላት ጋር አብሮ በመቆም የሚገኝ ስልጣን ሀገርን አያጸናም" ያሉት አማካሪ ሚኒስትሩ፣ በታሪክ ኢትዮጵያ ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት ሁሉ ከውጭ ጠላቶች ጋር የማበር አባዜ በተደጋጋሚ መከሰቱን አሳስበዋል።

የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ የውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን የሚገኝ ስልጣን የተረጋጋች ሀገር ሊፈጥር እንደማይችልና ዓላማውን እንደሚክሽፍ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ከማህበራዊ ሚዲያ ውዥንብር ውጭ የተደራጀ የነፍስ ወከፍ እንቅስቃሴ እንደሌለና ወታደራዊ ውጊያው መጠናቀቁን ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፣ ሕጋዊ እና ተቀባይነት ያላቸው የውስጥ ጥያቄዎችን በሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ መፍታት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን አስምረውበታል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

 

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: