በኢትዮጵያ 25 ሚሊየን የሚደርሱ አባወራ እና እማወራዎች እንዳሉ ይታመናል።
ከዚህ ውስጥ ግን ቀጥታ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት 5.2 ሚሊዮን አባወራዎች እና እማወራዎች መሆናቸውን መቅረቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።
ይህም የተደራሽነት ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፕሮሰስ እና ኳሊቲ ሥራ ማኔጅመት አስፈጻሚ አቶ እሱባለው ጤናው ከኤፍ ኤም አዲስ 97 .1 ጋር በነበራቸው ቆይታ ተቋሙ ረጅም ዘመናት በቂ የፋይናስ መንቀሳቀሻ ስላልነበረው አዳዲስ ሥራዎችን በሚፈለገውን ልክ መስራት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመንግስት ድጎማ ላይ የተመሰረተ ሆኖ መቆየቱ ለዘመናት አመርቂ ውጤት ሳያመጣ እንዲቆይ እንዳደረገው ያነሳሉ።
ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት የተዘረጉ በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማቶችም ስለመኖራቸውኝ ነው ያስረዱት።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት በርካታ ችግሮች እንዳሉበት የጠቆሙት አቶ እሱባለው ፤ ይህንንም ለማስተካከል የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች መሰራታቸውን አስታውሰዋል።
ተቋሙ በፋይናንስ እራሱን ችሎ እንዲቆም የማሻሻያ ሪፎርሙ አስፈላጊ እንደነበርም ገልጸዋል።
መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ስለመሆኑ የሚያነሱት አቶ እሱባለው ፤ በሪፎርሙ የሚገኘውን ገቢ በዋናነት ለሕብረተሰቡ ጥቅም በሚውሉ ሥራዎች ላይ እንደሚውልም ተናግረዋል።
ዘመን የዋጁ የቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ፋይናስ የግድ በመሆኑ፤ በሪፎርሙ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ አጠቃም ላይ ትሩረት በማድርግ የተሻለ ሥራ ለማከናወን ጥረት መደረጉንም አንስተዋል።
በሜሮን ንብረት