Search

11 የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጥምረት መሰረቱ

ረቡዕ ነሐሴ 14, 2017 92

በኢትዮጵያ በክልል ደረጃ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 11 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጥምረት መፍጠራቸውን አስታውቀዋል። 

ጥምረቱን የፈጠሩት ፓርቲዎች አገው ለፍትህና ዲሞክራሲ፣ አገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣  ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣  አፋር ነፃ አውጪ ግንባር፣ ጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣  የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ እንዲሁም የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ናቸው። 

ጥምረት የፈጠሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ ዓላማ ሀገራዊ ሰላምና መግባባትን መፍጠር፣ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ መስራት፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ማድረግ፣ ድምፅ ለሌላቸውና ድምፃቸው አልተሰማም ብለው ለሚያስቧቸው ዜጎች በጋራ ድምፅ መሆን፣ ትብብርን መሰረት ያደረገና መተሳሰብን ባካተተ መልኩ መስራት መሆኑም በምስረታው ወቅት ተገልጿል።

በምስረታ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ፥ ጥምረቱ ዜጎች በፓርቲዎች ላይ እምነት እንዳኖራቸው ከማድረጉም ባሻገር የዜጎችን ፍላጎት ለማርካት ያግዛል ብለዋ። 

አክለውም የፖለቲካ ልዩነትን ከማንፀባረቅ ባሻገር ለሀገር ረብ ያለው ነገር ለማበርከት እድል ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል። 

ኢቲቪ ያነጋገራቸው የጥምረቱ አባል የሆኑ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም፤ ጥምረቱ ሕብረተሰቡ ጋር ለመድረስና ዓላማችንን ለማስረፅ ያግዘናል ያሉ ሲሆን፤ በተደራጀ አቅም በዲሞክራሲያዊ ምርጫው ላይ ብቁ ተፎካካሪ እንድንሆን መደላድል ይፈጥርልናል ሲሉም ጠቅሰዋል። 

አክለውም አሁን ያለው የፖለቲካ ምህዳር ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጊዜያት አንፃር የተሻለ በመሆኑ፤ ጥምረቱ ለዓላማችን መሳካት በር ከፋች ነው ሲሉም ገልፀዋል። 

የተጣመሩት ፓርቲዎች የጋራ ስያሜያቸውን አስመልክቶ እያከናወኑ ያለውን የምስረታ ጉባዔ እንዳጠናቀቁ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል። 

በአሁኑ ሰዓት 60 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ፖርቲዎች ምክር ቤት ስር ተመዝግበው ይገኛሉ። 

ሳምሶን በላይ