መንግስት ያደረገው የመንግሥት ሠራተኞች ገቢ ማሻሻያ ውጤታማ ተጠቃሚነትን እንዲፈጥር፤ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያራምዱ ነጋዴዎችን መቆጣጠር ያስፈልጋል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሁሴን አሊ ገለፁ።
ማሻሻያው የሠራተኞቹን የመግዛት አቅም የሚያሳድግ በሌላ በኩል ነጋዴው ወደ ገበያው ለፍጆታ የሚያቀርበው ምርት መጠን እንዲያድግ የሚያስችል መሆኑንም ባለሙያው ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል።
ይህ የኢኮኖሚ መስተጋብሩን የሚያነቃቃ እና የሚያቀላጥፍ ሆኖ ሳለ፤ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ተመን የሚያስቀምጡ ከሆነ ውጤቱ የተገላቢጦሽ እንደሚሆን ነው ባለሙያው የተናገሩት።
ማሻሻያው ጥብቅ አስተዳደርን እንደሚሻ በመግለፅ ወደ ገበያው የሚገባው ገንዘብ ምርታማነትን የሚያበረታታ መሆን እንደሚገባው ገልፀዋል።
አክለውም በሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ሊደረግ የሚችል ትክክለኛ ያልሆነ የዋጋ ተመን፤ በጭማሪ የተገኘውን የሠራተኛውን ገቢ መልሶ ሊወስድ የሚችል በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው ሲሉም አፅዕኖት ሰጥተዋል።
መስከረም 2018 ዓ/ም ተግባራዊ የሚደረገው የደመወዝ ማሻሻያ የመንግስት ሠራተኞችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ሆኖም ሙሉውን የማህበረሰብ ክፍል የሚነካ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እና ምርት በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር መንቀሳቀስ፤ ከሕግ ተጠያቂነት እስከ ፍቃድ ክልከላ የደረሰ ርምጃ እንደሚያስወሰድ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
በአፎሚያ ክበበው