Search

አርሰናል ፈጥኖ የወሰነበት ኤቤሬቺ ኤዜ

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 126

አርሰናል ወደ ጎረቤቱ እና የምንጊዜም ተቀናቃኙ ቶተንሀም ሆትስፐር ሊያመራ ጫፍ የደረሰውን ኤቤሪቺ ኤዜን ለማስፈረም ከስምምነት መድረሱ ከሰዓታት በፊት የዓለም መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡
ከሁለት ቀን በፊት የክሪስታል ፓላስ ሊቀመንበር ስቴቭ ፓሪሽ እና የቶተንሀሙ አቻቸው ዳንኤል ሌቪ በዝውውሩ ጉዳይ በቀጥታ ከመከሩ በኋላ የኤዜ መዳረሻ ቶተንሀም ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ነገሮች በፍጥነት ተቀይረዋል፡፡
የጀርመናዊው አጥቂ ካይ ሀቨርዝ ድንገተኛ ጉዳት ሚካኤል አርቴታ የዝውውር መስኮቱ ሳይጠናቀቅ ሌላ መውጫ ቀዳዳ እንዲፈልግም አስገድዶታል፡፡
እግር ኳስን በአርሰናል ቤት ጀመረው የ27 አመቱ ኤቤሪች ኤዜ ዳግም ወደ አርሰናል በመመለስ መጫወት እንደሚፈልግ በተደጋጋሚ ሲናገር ቆይቷል፡፡
የጊዮኬሬሽን ዝውውር ጨምሮ ተጫዋችን ለማስፈረም ረጅም የድርድር ጊዜ የሚወስደው አርሰናል ኤቤሪቺ ኤዜን ወደ ሰሜን ለንደን ለማምጣት ግን 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ለክሪስታል ፓላስ ያቀረበው 60 ሚሊዮን ፓውንድ ተቀባይነት ስለማገኘቱ ይፋ ሆኗል፡፡
ባለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት በሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው አርሰናል የተሟላ ቡድን ሆኖ ለመቅረብ በዝውውሩ በንቃት እየተሳተፈ ሲሆን ለኤዜ ጥያቄውን ከማቅረቡ ተጫዋቹ ወደ አደገበት ክለብ መመለስ እንደሚፈልግ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ቀደም ብሎ ወደ ቶተንሀም ለማምራት በግል ጉዳይ ጭምር ስለመስማማቱ ቢዘገብም አሁን ግን ወደ ሌላኛ የሰሜን ለንደን ክለብ ለማምራት ከመድፈኞቹ ጋር በሁሉም የግል ጉዳዮች ተስማምቷል ተብሏል፡፡
አርሰናል ኤቤሬቺ ኤዜን የሚያግኘ ከሆን ምን አልባትም ጥያቄ እየተነሳበት ለሚገኘው የማርቲኔሊ ቦታ በቂ ምላሽ የሚያገኘ ሲሆን ሁለገቡ ተጫዋችም የሚፈልገውን ክለብ መለያ ዳግም የሚለብስበትን ዕድል ያገኛል፡፡
የትኛውም ዝውውር እስካልተጠናቀቅ ድረስ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ጀምስ ማዲሰንን በጉልበት ጅማት መበጠስ ጉዳት ለረጅም ጊዜ ያጣው ቶተንሀም ሌሎች አማራጮችን ይመለከታል ወይስ ደግሞ በዝውውሩ ፉክክር ውስጥ ይቆያል የሚለው በጥቂት ጊዜ ውስጥ መልስ የሚያገኝ ይሆናል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: