Search

በእናቱ ሆድ ውስጥ 10 ጊዜ ደም ተለግሶት የእናትን ጭንቀት ወደ ደስታ የቀየረው የተሳካ ሕክምና

ዓርብ ጥቅምት 21, 2018 71

በአፍሪካ ለመጀመሪያ በዓለም ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ግሩም የሕክምና ጥበብ የተስተዋለበት ሥራ የተከናወነው በኢትዮጵያ ነው።
በእናቱ ሆድ ውስጥ ብዙ ጊዜ ደም እየተለገሰው የነበረው ሕጻን በትናትናው እለት ወደዚህች ምድር በጤንነት ተቀላቅሏል፡፡
ወይዘሮ ሰናይት ታምራት ቀደም ሲል በነበረው እርግዝናዋ በተፈጠረባት የሾተላይ ችግር ምክንያት ልጇን አጥታለች፡፡
በጤና ጣቢያ ክትትሏን ታደርግ የነበረችው የ28 ዓመቷ ታካሚ፣ ቀደም ሲል በተፈጠረባት ችግር ምክንያት 'ዳግም ልጄን አጣው ይሆን' የሚል ከፍተኛ ጭንቀት ገብቷታል፡፡
ይህች እናት 21 ሳምንት ሲሆናት ክትትል ከምታደርግበት ጤና ጣቢያ በተፃፈላት ሪፈር መሰረት ወደ አበበች ጎበና እናቶች እና ህፃናት ማዕከል ታመራለች፡፡
የአበበች ጎበና የእናቶች እና የህፃናት ሕክምና ማዕከል ባደረገው ምርመራ ፅንሱ በሾተላይ ምክንያት የደም ማነስ እንዳጋጠመው ደረሰበት፡፡
ቀደም ሲል በሾተላይ ምክንያት ልጇን ላጣች እና አሁን በሆድዋ ለተሸከመችው ልጅ በጭንቀት ውስጥ ላለች እናት መፍትሔ ፍለጋ የተቋሙ ሰብ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ማድረግ ስለሚችሉት ነገር ምክክር ጀመሩ፡፡
ፅንሱ ገና የ21 ሳምንት መሆኑ የታሰበውን ሕክምና ከባድ አድርጎታል፡፡
በእናቱ ሆድ ውስጥ እያለ የደም ማነስ ችግር ላጋጠመው የ21 ሳምንት ብቻ ዕድሜ ላለው ፅንስ የደም ስሮቹ ደም ለመስጠት የሚያስቸግሩ ቀጫጭን ቢሆኑም፣ በማህፀን ውስጥ እንዳለ ደም የመስጠት ሕክምና ማድረግ ለፅንሱ ህልውና አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ ለታካሚዋ ተነገራት፡፡
የመጀመሪያው ደም የመለገስ ሕክምናም እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ተከናወነ። ታካሚዋ የመጀመሪያዎቹን ወራቶች በሳምት ሁለት ቀን ለክትትል ወደ ሕክምና ተቋሙ በማምራት አስፈላጊውን ክትትል ስታደርግ ቆየች፡፡
ፅንሱ ሕክምናውን እያገኘ መፋፋት እና እድገት ማሳየት ሲጀምር በሳምት አንዴ በመምጣት ክትትሉ ቀጠለ፡፡
ለእናት እና ለልጅ ጥብቅ የሆነ ክትትል በማድረግ ደም የመለገስ ሂደቱ እስከ 10 ጊዜ ቀጥሎ ፅንሱ የመወለጃው ጊዜ ሲደርስ በቀዶ ሕክምና 3.5 ኪ.ግ የሚመዝን ልጅ በሰላም ተገላግላ እናት ልጇን ማቀፍ ችላለች፡፡
በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ አበበች ጎበና እናቶች እና ህፃናት ሕክምና ማዕከል በትናንትናው እለት የተፈጠረው ይህ ታሪክ፣ በሕክምናው ታሪክ በዓለም በእናቱ ሆድ ውስጥ 10 ጊዜ ደም ተለግሶ ስኬታማ የሕክምና ክትትል በማድረግ ወደዚህ ዓለም የተቀላቀለ ሁለተኛው ልጅ ሆኖ ተመዝግቧል ፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ፅንስ በእናቱ ሆድ እያለ 10 ጊዜ ደም ተሰጥቶት የተሳካ የሕክምና ሂደት አልፎ የተወለደው በብራዚል ሲሆን፣ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያው የ21 ሳምንት ፅንስ በእናቱ ሆድ ውስጥ 10 ጊዜ ደም በመሰጠት ስኬታማ የሕክምና ሒደት አልፎ በስኬት የተወለደ መሆኑ ልዩ አድርጎታል፡፡
ሕክምናው በኢትዮጵያ ውስጥ በጳውሎስ ሆስፒታል፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና በየካቲት 12 የአበበች ጎበና የእናቶች እና ህፃናት ሕክምና ማዕከል የሚሰጥ ሲሆን 30 ሳምንት እና ከዛ በላይ የሆነ እድሜ ያለው ፅንስ የእናት ሆድ ውስጥ እንዳለ የመወለጃው ቀን እስኪቃረብ ድረስ ደም የመስጠት ሒደት የተለመደ ነው፡፡
በአሁን ሰዓት በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ አበበች ጎበና እናቶች እና ህፃናት ህክምና ማዕከል እናት እና ልጅ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ