ኢትዮጵያን የሚገባት ቦታ ለማድረስ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን ገለፁ። 
የኢትዮጵያውያን የመነጋገርና የመደማመጥ ባህል የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ያላት እንደመሆኗ የዘመናት የመንግሥት ሥርዓት የጎለበተባት ሀገር ናት ያሉት አምባሳደር መሐሙድ፤ በነዚህ ሂደቶች ውስጥ ቁስሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አንስተዋል።
እነዚህን ያለፉ ታሪኮች በይቅርታ እና በመተማመን በማለፍ ኢትዮጵያን የሚገባት ቦታ ማድረስ አለብን ብለዋል።
በአሜሪካ ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም፤ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አክለውም በዜጎች መካከል የአሸናፊነት እና የተሸናፊነት ስሜትን በማስወገድ መነጋገር እና መደማመጥ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለበት ዘርፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሀገር ሰላም ግንባታ ቅድሚያ መስጠት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ደግሞ የሰላም እና ልማት ጥናት ተመራማሪ ሮባ ጴጥሮስ (ዶ/ር) ናቸው።

ከመሳሪያ ይልቅ በሀሳብ ብልጫ ላይ የተገነባ የፖሊቲካ ባህልን በማጎልበት ለሀገር እድገት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በቢታንያ ሲሳይ
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            