Search

ትዕግሥት አሰፋ እና ዮሚፍ ቀጄልቻ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ዕጩ ሆኑ

ሰኞ ጥቅምት 17, 2018 70

የዓለም አትሌቲክስ በሁለቱም ፆታ የ2025 የዓመቱ የጎዳና ላይ ምርጥ አትሌት ዕጩዎችን ይፋ አድርጓል።

በዚህም አትሌት ትዕግሥት አሰፋ እና አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በዓመቱ በሁለቱም ፆታ ምርጥ ብቃት ካሳዩ አምስት አትሌቶች መካከል አንዱ ሆነዋል።

በሴቶቹ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ከኬንያውያኑ አትሌቶች ፔሬስ ጄፕቺርቺር እና አግኔስ ንጌቲች፣ ለኔዘርላንድስ ከምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሲፈን ሀሰን እና ከስፔናዊቷ ማሪያ ፔሬዝ ጋር ምርጥ አምስት ውስጥ ገብታለች።

በወንዶቹ ደግሞ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ከብራዚላዊው አትሌት ካይኦ ቦንፊን፣ ካናዳዊው አትሌት ኢቫን ዱንፊ፣ ኬንያዊው አትሌት ሳባስቲያን ሳዌ እና ከታንዛኒያዊው አልፎንስ ሲምቡ ጋር ምርጥ አምቱ ውስጥ ገብቷል።

አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በውድድር ዓመቱ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ የለንደን ማራቶን አሸናፊ መሆኗም ይታወሳል።

በተጨማሪም በሴቶች ብቻ (በሴት አሯሯጮች ብቻ) በተደረገው ማራቶን የዓለም ክብረ ወሰንን በእጇ ያስገባችበት ዓመት ሆኖ አልፏል።

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በበኩሉ በዓመቱ በ5ኪሎ ሜትር 6ኛውን የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን በ10 ኪሎ ሜትርም ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።

ከእነዚህ እጩዎች መካከል የዓመቱ ምርጥ አትሌትን ለመምረጥ በዓለም አትሌቲክስ ማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች ማለትም (በፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ኤክስ) ገጾች ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ክፍት መሆኑ ተገልጿል።

ድምፅ የመስጠት ሂደቱ የሚጠናቀቀው ኖቨምበር 2/2025 (ጥቅምት 23 ቀን 2018) መሆኑን እና አሸናፊው ይፋ የሚደረገው ኖቨምበር 30/2025 (ኅዳር 21 ቀን 2018) እንደሆነም ተመላክቷል።

በአንተነህ ሲሳይ

#ebc #ebcdotstream #WorldAthletics #AthleticsAwards