Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን የቀጥታ በረራ መጀመሩ የሀገራቱን ትብብር አጠናክሯል፡- የፓኪስታን ፕሬዚዳንት አሲፍ ዒሊ ዛርዳሪ

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 145

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን የቀጥታ በረራ መጀመሩ ሁለቱ ሀገራት በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ በቱሪዝምና በንግድ ያላቸውን ትብብር ማጠናከሩን የፓኪስታኑ ፕሬዚዳንት አሲፍ ዒሊ ዛርዳሪ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት አሲፍ ዒሊ ዛርዳሪ በፓኪስታን ከኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን የጀመረው የቀጥታ በረራ በሀገራቱ ቱሪዝምና ንግድ ዘርፍ ላይ ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
አክለውም ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ ሀገራቸው ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ለምታደርገው ትብብር አጋዥ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉትን ለውጦችና ስኬቶች በአካል ለመመልከት እና እያደገ የመጣውን አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር በቅርቡ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በሕግ ዘርፎች ያደረገችው መሰረታዊ ማሻሻያዎች ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግሩ ስለመሆናቸው አስረድተዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ በቱሪዝም፣ በንግድ፣ በግብርና እና በባንክ ዘርፎች ያለውን ሰፊ አቅም በማውጣት ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹና ማራኪ ሁኔታን እንደፈጠረ አንስተዋል።
ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያስገኘላትን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ስኬት ተሞክሮን ለፓኪስታን ማጋራቷ ለኢትዮጵያ ኩራትና የትብብር መገለጫ ስለመሆኑ አምባሳደር ጀማል ለፓኪስታኑ ፕሬዚዳንት ገልጸውላቸዋል።
በሰዒድ ዓለሙ