Search

ማኀበራዊ ሚዲያን ለበጎ አድራጎት የሚጠቀመው ታዋቂው ዩቱዩበር

ሓሙስ ነሐሴ 15, 2017 3758

424 ሚሊየን የዩቱዩብ ሰብስክራይበሮችን በመያዝ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የለውም።

... ግንቦት7 ቀን 1998 አሜሪካን ካንሳስ ውስጥ የተወለደው አሜሪካዊው ዝነኛ ዩቲዩበር ጂሚ ዶናልድሰን (ሚስተር ቢስት) የመጀመሪያ የዩቲዩብ ቪዲዮውን የሰራው 13 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር።

ሆኖም የእውቅናው ማማ ላይ ለመውጣት በርካታ ዓመታትን ፈጅቶበታል። ጂሚ ዶናልድሰን አሁን ላይ ከዩቲዩበርነቱ ባልተናነሰ በበጎ ምግባሩ የሚጠቀስ 27 ዓመት ወጣት ነው።

 

 

በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በማኀበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ የሚሰራው ሚስተር ቢስት በስሙ የሚጠራ የበጎ አድራጎት ተቋም አማካኝነት እስካሁን 50 ሚሊየን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ  ወጪ በማድረግ የተለያዩ መልካም ተግባራትን አከናውኗል።

ኮምፒውተሮችን እና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ያሟሉ ትምህርት ቤቶች፣  ለወጣቶች የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ ሆስፒታል እና የጤና ተቋማትን አስገንብቷል።

አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ሰዎች በሚሊዮኖች ዶላር በማውጣት የምግብ እርዳታ አድርጓል።  

የተቀናጡ ግዙፍ ቪላዎችን ከመግዛት እና ሚሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ አስር መኪኖችን ከመቀያየር ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችሉ የዩቲዩብ ቪዲዮዎችን መስራት እንደሚመርጥ የሚናገረው ዶናልድሰን ማኀበራዊ ሚዲያን ለበጎ ተግባር ለማዋል እና የደግነት እጁን ለመዘርጋት ውቅያኖስ አያግደውም ይባልለታል።

በደቡብ አሜሪካ፣ በኤዥያ፣፡ በአፍሪካ እና በተለያዩ አህጉራት የልግስና እጁ ደርሷል። በዚህ የበጎ አድራጎት ሥራው በአፍሪካ በተለያዩ ሀገራት ራሱ በአካል እየተገኘ ለመጠጥ የሚሆን የውሃ ጉድጓድ  አስቆፍሯል።

በዚህም በካሜሩን፣ በዚምባቡዌ፣ ኡጋንዳ እና ኬንያ ለሚገኙ የገጠር ከተሞች ለዓመታት የሚያገለግሉ እና ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አንድ መቶ የውሃ ጉድጓዶችን አስቆፍሮ ለአካባቢው ነዋሪዎች አስረክቧል።

በአንድ የኬንያ የገጠር መንደር በተገኘበት ወቅት ለደህንነት አስጊ የሆነ አሮጌ የእንጨት ድልድይን አስፈርሶ ዘመናዊ ድልድይ አስገንብቷል።

በኤልሳልቫዶር፣ ጃማይካ እና አርጀንቲና ውስጥ ለሚገኙ ችግረኞች አንድ መቶ ቤቶችን ገንብቶ የቤት እቃዎችን አሟልቶ ሰጥቷል።

 

 

በአሜሪካ እና በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሶስት የአካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ እግር እንዲያገኙ አድርጓልበደቡብ አፍሪካም ወላጆቻቸውን ላጡ ልጆች ቤት ሰርቶ ሰጥቷል።

ይህ ብቻም አይደለም በኤዥያ በህንድ በዓይን በሽታ እይታቸውን ላጡ አንድ ሺህ ሰዎች ሙሉ የዓይን ቀዶ ሕክምና ወጪ በማድረግ እይታቸው እንዲመለስ ረድቷል።

በፊሊፒንስ የመስማት ችግር ለነበረባቸው ሰዎች ቀዶ ክምና ወጪ በማድረግ ጤናቸው እንዲመለስ አድርጓል።

በአሜሪካ በምግብ ራሳቸውን ላልቻሉ እና በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ሰጥቷል።  በተለያዩ የአሜሪካ ከተማ ለሚኖሩ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርጓል።

 

 

የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ አብረውት ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ ሀገራት 23 ሚሊየን ችግኞችን እንዲተከሉ ሰርቷል።

በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የባህር ዳርቻዎችን በማፅዳት 33 ሚሊየን ፓውንድ የሚመዝኑ የተጣሉ ፕላስቲኮችንና ቆሻሻዎችን እነዲጸዱም ረድቷል።

እድሜውን በሙሉ በዚህ መሰል የበጎ አድራጎት መቀጠል እንደሚፈልግ የሚናገረው ሚስተር ቢስት በዩቱዩብ ሰብስክራይበር ብዛት ተወዳዳሪ በሌለው ቻናሉ እ.አ.አ. 2024 ከዩቲዩብ ብቻ 85 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችሏል።

የሀብቱ መጠንም አንድ ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የቅርብ ጊዜ የፎርብስ ዘገባ አመላክቷል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ