Search

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ፤ የማድረግ አቅምን ወደ ዓለም መድረክ

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 73

ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነቷ የምትከተለውን አቅጣጫ በብሔራዊ ጥቅም፣ በሉዓላዊነት እና በቀጣናዊ ትብብር መርሆዎች ላይ በማጠናከር፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሳትፎ እያሰፋች ትገኛለች።

የዲፕሎማሲው አቅጣጫም ከቃል እና ከውጭ ድጋፍ ጥያቄ ባለፈ፣ የሀገራችንን የማድረግ አቅም በተጨባጭ ውጤቶች ላይ ለመመሥረት ያተኮረ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀገራችንን ከጥገኝነት እና ከሌሎች አጀንዳዎች ተቀባይነት በማላቀቅ፣ ታሪኳን፣ ነፃነቷን እና እያደገች ያለችበትን ፍጥነት የሚመጥን ተጽዕኖ ፈጣሪ የዲፕሎማሲ ቁመና እንድትገነባ ያለመ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ይህ ማዕቀፍ በአራት ዓበይት መርሆዎች የሚመራ ሲሆን፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ንቁ ተሳታፊ፣ ከአንድ የፖለቲካ ጎራ ብቻ ሳትወሰን አማራጭ ዲፕሎማሲን የምትከተል፣ ፈጣን የጂኦፖለቲካ ለውጦችን በጥበብ በመከታተል ከሁኔታዎች ጋር ተላማጅ እና የሌሎችን ፍላጎት ከመቀበል ይልቅ ብሔራዊ ጥቅሟን የምታስከብር አጀንዳ ቀራጭ በመሆን ስትራቴጂያዊ ራስን የመቻል መንገድ እንድትቀይስ አድርጓታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የBRICS አባልነት ከዚህ አቅጣጫ ጎልቶ ከሚታይ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ አንዱ ነው። አባልነቱ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የዓለም ኃያላን እና ታዳጊ ኢኮኖሚዎች ጋር ያላትን ግንኙነት በማስፋት፣ በንግድ፣ በፋይናንስ እና በልማት ትብብር የበለጠ አማራጭ እንዲኖራት ያደርጋል።

በቀጣናውም ኢትዮጵያ የጎረቤት ሀገራትን ጥቅም ከሀገራችን ልማት ጋር በማስተሳሰር የትሥሥር አቅጣጫን እያስፋፋች ነው።

የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ እና የድንበር ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶች ኢኮኖሚያዊ ትሥሥርን ከማጠናከር ባለፈ፣ የጋራ ልማትን ለማስፋፋት የሚያገለግሉ የዲፕሎማሲ መሣሪያዎች ሆነዋል።

በዓባይ ጉዳይ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያም ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊ ድርድር፣ በትብብር እና በፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም መርሆዎች ላይ በመመሥረት አራምዳለች።

ግድቡ መጠናቀቁም የሀገራችንን የማስፈጸም አቅም ከማሳየት ባለፈ፣ በቀጣናው የጋራ ብልጽግና ዕድልን የሚያሰፋ ፕሮጀክት ሆኖ ቀጥሏል።

የባሕር በር ጉዳይም በዲፕሎማሲው ዋና የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች መካከል ተካቷል። ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በሰላማዊ ውይይት፣ በጋራ ጥቅም እና በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች ላይ በመመሥረት እያቀረበች ነው።

ይህም የሀገራችንን የረጅም ጊዜ ጥቅም በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ጥረት ያሳያል።

ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ እስያ ያላትን የዲፕሎማሲ አድማስ በማስፋት ላይ ትገኛለች። ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ከሕንድ፣ ከቻይና፣ ከጃፓን እና ከሌሎች የእስያ ሀገራት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ እና በልማት ትብብር ዙሪያ እየጠነከሩ መጥተዋል።

በዚህ ሂደት የዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅምም እየተሻሻለ የሀገራችንን የልማት ሥራዎች፣ ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንት እና የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎች በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠረ ነው።

የዲፕሎማሲ አቅሟንም በኢኮኖሚ፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በንግድ እና በመሠረተ ልማት ትስስር እያሰፋች ትገኛለች።

የዘመኑ ዲፕሎማሲም ከባህላዊ የመንግሥታት ግንኙነት ባለፈ ዲጂታል መድረኮችን፣ የሕዝብ ዲፕሎማሲን እና የሀገር ገጽታ ግንባታን የሚያካትት እየሆነ ነው። የሀገራችንን የልማት ሥራዎች፣ ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና የተለያዩ የሀገር አቅሞችን ለዓለም ማስተዋወቅም የዚሁ ጥረት አካል ነው።

 የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በቃል ከመግለጽ ወደ ተግባር የማሳየት አቅም እየተሸጋገረ የሚታይበት ሂደት ነው። የBRICS አባልነት፣ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስር፣ የዓባይ ጉዳይ፣ የባሕር በር አጀንዳ እና የአፍሪካ አህጉራዊ ዲፕሎማሲ በተለያዩ መስኮች የሀገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ጥረት ያሳያሉ።

በኢንቲሃድ አብራር

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: