Search

ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 113

ዛሬን ጠምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 2ኛው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ጉባኤ ተጠናቅቋል።

ጉባኤው በሀገራችን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የውጭ ምንዛሬ ተመን ማሻሻያ እንዲሁም በዋጋ ንረት እና በፋይናንስ ዘርፉ ተደራሽነት ላይ ምክክር አድርጓል።

በዛሬው የማጠቃለያው ውሎው ደግሞ ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አገልግሎት ስትራቴጂ ይፋ ተደርጓል።

ይህም የፋይናንስ ተደራሽነትን በማረጋገጥ እና ሀብትን በማንቀሳቀስ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል።

ስትራቴጂው ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ዘርፉ ከተበታተነ እና በባንክ ላይ ብቻ ከተመሠረተ አሠራር ወጥቶ፣ በቅንጅት የሚመራ፣ ተወዳዳሪ፣ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው እና ለፋይናንስ አካታችነት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ ነው። 

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፥ በኢትዮጵያ ላለፉት አሥርት አመታት ከተካሄዱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦች እጅግ ጉልህ የሆነው የውጭ ምንዛሬ ተመን (ፎሬክስ) ማሻሻያ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።

በሀገራችን ዲጂታል ክፍያዎች እና የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ከሳይበር ጥቃቶች ለመጠበቅ ጠንካራ የቁጥጥር እና የደህንነት እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ዶ/ር ኢዮብ አስታውቀዋል።

በመድረኩ እንደተብራራው፥ በሕጋዊው እና በትይዩ (ጥቁር) ገበያ መካከል ያለው የምንዛሬ ልዩነት አሁን ላይ በእጅጉ ቀንሷል። በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚፈስሰው የውጭ ምንዛሬ መጠንም ወደ 37 ቢሊዮን ዶላር አድጓል።

በበጀት ዓመቱ የወጪ ንግድ ገቢ 11.2 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 8 በመቶ ይሸፍናል። ይህም ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበ ከፍተኛው አፈጻጸም ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ማሻሻያው ኢትዮጵያን ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተጠቅሷል።

በብሩክታዊት አስራት

#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: