Search

ከወጪ ንግድ 8.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

ዓርብ ነሐሴ 16, 2017 126

ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 8.3 ቢሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ ማግኘት መቻሏን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት ግምገማ "በተሳለጠ ንግድ ወደ ሚጨበጥ ሀገራዊ ተስፋ" በሚል በተዘጋጀ የንግድ እና ቀጠናዊ ሴክተር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነው።
በበጀት ዓመቱ በሀገር ውስጥ ንግድ በበይነ መረብ (ኦን ላይን) አገልግሎት በተሰራው ስራ ለ3 ሚሊዮን የንግዱ ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት መቻሉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በሕገ ወጥ ንግድ የተሰማሩ እና ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር ባደረጉ 110 ሺህ ነጋዴዎች ለይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
የዋጋ ንረትን ለመከላከል አዳዲስ የቅዳሜ እና እሁድ የገበያ ማዕከላትን ወደ ስራ በማስገባት ሰፊ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።
በዉጪ ንግድ ግኝት 8.3 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ያነሱት ሚኒስትሩ በእያንዳንዱ ዘርፍ ማንሰራራት የታየበት ዓመት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በተደረገዉ ድርድር አመርቂ ውጤት መመዝገቡ የተገለፀ ሲሆን፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና በመጪዉ ዓመት መስከረም ወር እንደሚጀመር ተገልጿል።
የክልል የንግድ ቢሮ ኃላፊዎች በበጀት ዓመቱ የተሰሩ ሥራዎች ሪፓርት በግምገማ መድረክ ያቀረቡ ሲሆን፣ በሪፖርቶቹ ላይ በመወያየት እና ለ2018 በጀት ዓመት በተያዙ እቅዶች ለይ የመግባቢያ ስምምነት በማድረግ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በምንተስኖት ይልማ