የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ የሚገኙና ለህዝብ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት ፕሮጀክቶች በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የገበያ ማዕከላት፣ የመኪና ማቆሚያዎች እና የህፃናት መዝናኛዎች ናቸው።
ከለገሃር ሜክሲኮ አፍሪካ ህብረት ድረስ በአንድ ጊዜ ከ3 ሺህ 700 በላይ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚያስችሉ 23 የፓርኪንግ ስፍራዎች እና ተርሚናሎችም ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
በምርቃቱ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ግዙፍ የልማት ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
በተለይ ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል በአራዳ ክ/ከተማ የሚገኘው ስኬት የገበያ ማዕከልና የመኪና ማቆሚያ፤ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ሌሎች ትልልቅ ጉባኤዎች ሲካሄዱ መተላለፊያ የነበረና የከተማዋን ውበት የማይመጥኑ ገፅታዎች እንደነበሩበት ከንቲባዋ ተናግረዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች አማራጭ የገበያ ማዕከል፣ ምቹ የመኪና ማቆሚያ እና የህፃናት መጫወቻ አገልግሎትን ከማቅረብ ባሻገር ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንደሆኑ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ከ19 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች መከናወናቸውም ተመላክቷል።
በዘሃራ መሃመድ
#ebc #ebcdotstream #AddisAbaba