Search

በኢሉአባቦር ዞን ከ 500 ሺህ ኪሎግራም በላይ የአቮካዶ ምርት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው

ቅዳሜ ነሐሴ 17, 2017 39

በኢሉአባቦር ዞን በተያዘው የምርት ዘመን ከ500 ሺህ ኪሎግራም በላይ የአቮካዶ ምርት ለአለም ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የኤክስፖርት ምርቶችን በስፋት በማምረት የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ የተያዘውን አገራዊ ግብ ለማሳካት በዞኑ ለመጀመርያ ጊዜ 500 ሺህ ኪሎግራም የአቮካዶ ምርት ለአለም ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኢሉአባቦር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሀመድጠሀ አባፊጣ፤ በዞኑ ከቡና እና ማር ቀጥሎ ለመጀመርያ ጊዜ አቮካዶን ለአለም ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ አሁን ላይ በይፋ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

በዞኑ የምግብ ሉአላዊነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የኤክስፖርት ምርቶችን በማስፋት የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ተናግረዋል፡፡

የመርሀግብሩ አንድ አካል የሆነውና ተግባራዊ በመደረግ ላይ በሚገኘው የአቮካዶ ልማት ኢኒሼቲቭ የተያዘውን ግብ ለማሳካት አርሶአደሩ የተሻሻሉ ምርታማ ዝርያዎችን  እንዲጠቀም የሚያግዝ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ መሀመድጠሀ  ገልፀዋል፡፡

በዞኑ የበቾ ወረዳ አርሶአደሮች ከአሁን በፊት አቮካዶን በጓሮ በማልማት በአካባቢው ገበያ  ተገድበው ሲያቀርቡ በመቆየታቸው በድካማቸው ልክ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ ግን ምርጥ የአቮካዶ ዝርያን ማልማት በመጀመራቸው ለአለም ገበያ ለማቅረብ በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር የበለጠ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በሚፍታህ አብዱልቃድር

#EBC #ebcsotstream #Avocado #Agriculture