በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙ ሕንፃዎች ከታች ደግሞ ለግለሰቦችና ለድርጅቶች ተከራይተው አገልግሎት ሲሰጡ ማየት የተለመድ ተግባር ሆኗል፡፡
በጉዳዩ ላይ የሕንፃ አጠቃቃም አዋጅ ቁጥር 624 እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው 243/2003 መመሪያ መኖሩን የሚናገሩት ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ አዲስ መሀመድ፤ ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም የህንፃ ሹም ፍቃድ ማግኘት አለበት ይላሉ፡፡
በግንባታ ላይ ያለ ሕንፃ ከታች አገልግሎት እንዲሰጥ ፍቃድ መስጠት በሕንፃዎች አጠቃቀም አዋጁም ሆነ በመመሪያው አይቻልም ሲሉም የሕግ አማካሪዋ ለኢቢሲ ተናግረዋል።
ያላለቀ ሕንፃን ወደአገልግሎት ለማስገባት በቅድሚያ የሕንፃው ባለቤት መስፈርቶችን ካሟላ መሰረታዊ መረጃዎችን በመያዝ ሕንፃው ለአገልግሎት ብቁ ነው ለመጠቀም ፍቃድ ይሰጠኝ ብሎ ለሕንፃ ሹም አካል ማመልከት እንዳለበት አስረድተዋል።
የሚመለከተው የሕንፃ ሹም ደግሞ ጥያቄው በደረሰው በአስር ቀናት ውስጥ የሕንፃውን ሁኔታ በማየት ለመገልገያነት እንደሚውል ወይም ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው መልስ መስጠት እንዳለበት ሕጉ ያስገድደዋል ይላሉ።
ሕንፃው ያላሟላቸው ቅድም ሁኔታዎች ካሉም በመግለፅ ለአገልግሎት ብቁ አለመሆኑን መልሰ መስጠት ይጠበቅታል ነው ያሉት የሕግ አማካሪዋ፡፡ የሕንፃ ባለቤቶች በዚህ መንገድ ግንባታው ያልተጠናቀቀን ሕንፃ እንደሚያከራዩም ተናግረዋል፡፡
በግንባታ ላይ ያለ ሕንፃን ግን አገልግሎት መስጠት እንዳይችል የሚያዝ አዋጅ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
ሕንፃዎች ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ በልዩ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ ከተፈለገ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በግንባታ ላይ ያለው ሕንፃ ከታች አገልግሎት እየሰጠ ከላይ በግንባታ ላይ መሆኑ በማንኛውም ሁኔታ ጉዳት ማያደርስ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ተቆጣጣሪ እና ፍቃድ ሰጪ አካላትም ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ በወንጀልም በፍትሐብሄርም ተጠያቂ እንደሚሆኑ በሕግ መቀመጡን ጠበቃና የህግ አማካሪዋ ተናግረዋል፡፡
በላሉ ኢታላ
#EBC #ebcdotstream #Law #construction