በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ካፋ እና ኮንታ ዞኖች የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቶ 10 ሰዎች ሞተዋል በሚል የተሰራጨው መረጃ ሐሰት መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።
የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ለማ መሰለ (ዶ/ር)፥ በክልሉ ካፋ እና ኮንታ ዞኖች በ18/12/2017 በጣለው ከባድ ዝናብ የመሬት መንሸራተት ተከስቶ የሰው ሕይወት አልፏል በሚል የተሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል።
በክልሉ ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው በተለዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል።
አሁን ላይ እየጣለ ካለው ዝናብ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመከላከል ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠራ አንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር ለማ፤ ዜጎችም ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
እንደዚህ ዓይነት የውሸት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም ዶ/ር ለማ አሳስበዋል።
በሰለሞን ባረና
#ኢቢሲዶትስትሪም #ደቡብምዕራብኢትዮጵያ #ካፋ #ኮንታ