ታደሰ ቶርዱ ይባላል። የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ሲሆን፤ በልብስ ስፌት ሥራ ተሰማርቶ ይተዳደራል። በቅድሚያ ተቀጥሮ በመሥራት የልብስ ስፌት ሙያውን አዳብሯል።
ገንዘብ በመቆጠብም በኋላ ላይ የራሱን የልብስ ስፌት ድርጅት ከፍቶ በሙያው መሥራት ጀምሯል። ሥራውን ለማስቀጠልና ለማስፋት ግን የገንዘብ እጥረት ፈታኝ ሆኖበት ነበር።
ይህን ችግር ለማለፍ በቁጠባ እና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት አባል ሆኖ በየሳምንቱ በመቆጠብ ብድር ወስዶ ሥራውን ማስቀጠልና ማስፋት ችሏል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው ምኞቴ ተሰራ አነስተኛ የጥፍር ማስዋቢያ ትምህርት ቤት አላት። ቅድሚያ በጥፍር ማስዋም ሙያ ለ7 ዓመታት ሠርታለች።
የቁጠባ ባህሏን አሳድጋ በመቆጠብ ላይ ስትሆን፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ብድር ወስዳ ሥራዋን ለማስፋት አቅዳ እየሠራች ትገኛለች።
የሁሉ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ከ10 ብር ጀምሮ መቆጠብ የሚችል ማንኛውም ሰው አባል የሚሆንበት ተቋም መሆኑን የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መሳፍንት ደበበ ይናገራል።
በሁሉም የሥራ ደረጃ ያሉ ሰዎች መቆጠብ እንደሚችሉ እና ማህበሩም በአጭር ጊዜ ብድር እንደሚያቀርብ ይገልፃል።
ማህበሩ የብድር አገልግሎት ለመስጠት ንብረት ማስያዝ እና ሌሎች መስፈርቶችን እንደማይጠይቅም አቶ መሳፍንት አክሎ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን የልማት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ሺሰማ ገ/ሥላሴ በበኩላቸው፥ መቆጠብ ትልቅ ዋጋ እንዳለው፤ በመቆጠብ ሁሉም ሰው መሻሻል እንደሚችል አፅንዖት ሰጥተዋል።
በቢታንያ ሲሳይ
#ኢቢሲዶትስትሪም #ሥራፈጠራ #ቁጠባ