Search

ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ረቡዕ ጥቅምት 11, 2019 56

ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በዚሁ ዙሪያ ከንቲባዋ በፌስቡክ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያጋሩት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተናል!

በከተማችን በመሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችና በቤት ኪራይ ላይ እየታዩ ያሉ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠርና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል እየተወሰዱ ባሉ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርገናል።

በውይይቱ የሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ የዳቦ፣ የታሸገ ውኃና የቤት ኪራይ ዋጋዎች ላይ የሚታዩ ያልተገቡ ጭማሪዎች ተገምግመዋል። ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን ለማረጋገጥም የሚከተሉት ዋና ዋና እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።

1. የምርት አቅርቦትን ማሳደግ

የመሠረታዊ ፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት በመጨመር የዋጋ መረጋጋትን ለማምጣትና ሸማቹ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን።

2. የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትና የደላላ ሰንሰለትን ማሳጠር

አምራቾችንና ሸማቾችን በቀጥታ የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላትን በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ በማቋቋም ምርቶች በቀጥታ ለሸማቾች እንዲቀርቡ እየሠራን ነው። ሕብረተሰቡም ከእነዚህ የገበያ ማዕከላት በመገበያየት የተመጣጣኝ ዋጋ አማራጮችን እንዲጠቀም እናበረታታለን።

3. የሸማቾች ማኅበራትን ማጠናከር

የሸማቾች ማኅበራት የምርት አቅርቦትና ጥራት እንዲያድግ ተጨማሪ 500 ሚሊዮን ብር የሚያዝ ተዘዋዋሪ ፈንድ (Revolving Fund) መድበናል።

4. የእሑድ ገበያዎችን ማስፋፋት

ሸማቾች መሠረታዊ የዕለት ተዕለት ፍጆታዎቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ የእሑድ ገበያዎችን እናስፋፋለን፤ አቅርቦታቸውንም እናጠናክራለን።

5. ቁጥጥርንና የሕግ ማስከበርን ማጠናከር

የገበያ ሥርዓትን በሚጥሱና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ሥራችንን እናጠናክራለን።

6. የቤት ኪራይን በተመለከተ የአከራይና የተከራይ ግንኙነት በሕግ፣ በውል ስምምነትና በጋራ ኃላፊነት መመራት አለበት። ዜጎች መብታቸውን በሕጋዊ መንገድ እንዲያስከብሩና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማስረጃ እንዲያቀርቡ እናበረታታለን። በተመሳሳይም ተደራሽና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ማሳደግ ዘላቂ መፍትሔ እየተሰራ ነዉ።

በውይይታችንም የአቅርቦት ችግሮችን ከመሠረቱ በመፍታት፣ ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በማረጋገጥና ሕገወጥ የዋጋ ጭማሪዎችን በመቆጣጠር የዜጎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በጋራ ለመሥራት ተስማምተናል።

ሕብረተሰቡ አስተዳደሩ ባመቻቻቸው የሸማቾች ማኅበራትና የእሑድ ገበያዎች በመገበያየት የኑሮ ወጪውን እንዲቀንስ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

በተጨማሪም ዜጎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ወይም የገበያ ሕግ ጥሰት ሲያጋጥማቸው በቂ ማስረጃ በማቅረብ ለሚመለከተው የከተማ አስተዳደር አካል ሪፖርት እንዲያደርጉ፣ ከተረጋገጠ መረጃ ውጭ ወሬዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን በጋራ እንዲደግፉ አሳስባለሁ።

የዜጎችን የኑሮ ጫና ማቃለልና ፍትሐዊ የገበያ ሥርዓትን ማረጋገጥ የጋራ ኃላፊነታችን ነው!

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: