ለታሪካዊቷ ጎንደር እና ለአካባቢዋ ማኅበረሰብ ትልቅ የምሥራች የሆነው የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አስመልክቶ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ባሰፈሩት መልዕክታቸው እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ለረጅም ዓመታት የዕቅድ እና የአተገባበር መጓተት ቢፈታተነውም፣ በመደመር እሳቤ የአፈጻጸም ችግሮቹን በመፍታት ወደ ታላቅ በረከት መለወጥ ተችሏል።
የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ያሉት ዋና ዋና ሁለንተናዊ ጥቅሞች፦
የመስኖ ልማት እና የአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት፦ ግድቡ 185 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፤ ከ17 ሺህ ሔክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት በአካባቢው የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ ያደርጋል።
የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እና የኢኮኖሚ መነቃቃት፦ ለጎንደር ከተማ እና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች አስተማማኝ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ከማቅረቡ ባለፈ፣ የአካባቢውን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት በመመለስ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ፈጥሯል።
የሥራ ዕድል እና የቱሪዝም ልማት፦ በግድቡ ሰው-ሠራሽ ሐይቅ ዙሪያ የሚስፋፉት የከተማ ግብርና፣ መጠነ-ሰፊ የዓሣ እርባታ፣ እንዲሁም ለቱሪዝም ልማት የሚሆኑ የመዝናኛ ሪዞርቶች እና ሎጆች ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እና የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያሳድጉ ናቸው።
ይህንን ስኬት ለዕይታ ለማብቃት በጥብቅ ክትትል እና ድጋፍ እውን ማድረግ የተቻለ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ጎንደር ገና ብዙ ሊሠራላት የሚገባ ከተማ እንደመሆኗ ሕዝቡ በልማቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ ዕድገት ሁሉንም አካባቢዎች ያካተተ እና ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያቅፍ እንዲሆን የፌዴራል መንግሥት በትጋት መሥራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: