የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወ/ሥላሴ ባለአደራ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ባለአደራ አስተዳደሩ የመጀመሪያ ሥራው ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረግ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ረዳኢ በመቀሌ የተጀመረው ይህ መድረክ በተለያዩ አከባቢዎች እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
አቶ ረዳኢ በመግለጫቸው እንዳሉት በቅርቡ ከተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ስራ ይጀመራል።
ከዚህ ቀደም ከጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተወስኖ እንደነበር ያነሱት አቶ ረዳኢ ተፈናቃዮች ከተመለሱ አጀንዳ የሚያጣው ህገወጡ የህውሃት ቡድን ይህ እውን እንዳይሆን አድርጓል ብለዋል።
ከፌዴራል መንግሥት ጋር ስምምነት ተደርሶ ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ የተፈለገ ቢሆንም ህገወጥ ቡድኑ ግን የእኔ ካድሬ አብሮ ካልገባ ፣ የእኔ ሚሊሻ አብሮ ካልገባ እነሱ አይመለሱም በማለት ተፈናቃዮችን እንደ መያዣ መጠቀሙን አስታውሰዋል።
ተፈናቃዮችን እንደ መያዣ የተጠቀመው አካል አሁን ላይ በመረጠው መንገድ እየጠፋ በመሆኑ ተፈናቃይ ወገኖች ሰብዓዊ መብታቸው በተጠበቀ መንገድ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል የትግራይ ክልል የፊዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ወደሥራ ቦታቸው በመሄድ ሪፖርት አድርገው ሥራቸውን እንዲጀምሩ አሳስቧል።
ወንድወሰን አፈወርቅ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: