ኢትዮጵያ ከ60 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ሊታረስ የሚችል ለም መሬት፣ ሰፊ የውኃ ሀብት፣ ተስማሚ የአየር ንብረት እና ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያላት፣ ለዘመናት በዝናብ ጥገኝነት እና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ዘይቤ ምክንያት ለስንዴ ግዢ ብቻ በዓመት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ታወጣ ነበር።
ይህንን የድኅነት እና የጥገኝነት ታሪክ ለመቀየር የመደመር መንግሥት የቀረጸው አዲሱ የግብርና ፖሊሲ፣ ዘርፉን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ተችሏል።
ለዚህ ስኬት የኩታ ገጠም እርሻ፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቮች በዋና ዋና ስትራቴጂነት ተተግብረዋል።
በእነዚህ ስትራቴጂዎች አማካኝነት በሙዝ ልማት ከአንድ ሔክታር በዓመት ከ400 ኩንታል በላይ ምርት በማግኘት፣ የአንድ አርሶ አደር ዓመታዊ ገቢ እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር አድጓል።
ይህ አዲስ አሠራር በ2018 በጀት ዓመትም አበረታች ውጤት አስመዝግቧል። ከ29 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት በማረስ 1.3 ቢሊዮን ኩንታል ምርት የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከውጭ ንግድ ከተገኘው 11.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛውን ድርሻ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ማስገኘት ችሏል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል 20 ሺህ ሔክታር ብቻ የነበረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ወደ 3.6 ሚሊዮን ሔክታር በማደጉ፣ በበጋ እና በክረምት በድምሩ 280 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል።
ከዚህ ባሻገር ቀደም ሲል ግብርና ባልተለመደባቸውና በተደጋጋሚ በድርቅ በሚጠቁ እንደ አፋር፣ ሶማሊ እና ቦረና ባሉ አካባቢዎች የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር ውኃን በመጠቀም አዲስ ታሪክ ተጽፏል።
ለምሳሌ በቦረና ቀደም ሲል 90 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በሴፍቲኔት ዕርዳታ ይኖር የነበረበት ሁኔታ ተቀይሮ አሁን ላይ ወደ ዜሮ መውረድ ችሏል።
በሌላ በኩል በከተማ እና በገጠር የቤት ጓሮዎችን በመጠቀም የተጀመረው የሌማት ትሩፋት በእንቁላል፣ በማር እና በወተት ምርት ላይ ከፍተኛ እመርታ በማስመዝገብ የዜጎችን የምግብ ሥርዓት አሻሽሏል።
ከዚህም ባሻገር ዘርፉ በበጀት ዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ከሴፍቲኔት ዕርዳታ ጥገኝነት አላቅቆ ራሳቸውን ወደ መቻል አሸጋግሯል።
ይህ ከልመና ወደ ማምረት የተደረገ ታሪካዊ ጉዞ፣ ኢትዮጵያ በምርት እና በስራ የቆመች #ትልቅሀገር፣ በራሷ አቅም የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች #ትልቅሕዝብ እና ለዘላቂ ብልጽግና የተዘረጋ #ታላቅርዕይ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: