ከቀጨኔ እስከ ባምቢስ እና እስከ ሰላም መንገድ ድረስ የተከናወነው ግዙፍ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ዛሬ በይፋ ተመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ሰርዓቱ ላይ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክቱ "አይቻልም" የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሮ በራሳችን አቅም ተአምር መፍጠር እንደሚቻል የታየበት ትልቅ ምዕራፍ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከንቲባዋ እንደተናገሩት፤ የአዲስ አበባ ወንዞች ተፈጥሮአዊ ማንነታቸውን አጥተው የብክለት መነኸሪያና የበርካታ በሽታዎች ምንጭ ሆነው የቆዩ ቢሆንም፣ ዛሬ የተመረቀው መሰረተ ልማት ግን የነዋሪዎችን ጤና ከመጠበቁ ባሻገር የከተማዋን መልሶ ማልማትና ምህዳራዊ ውበት እውን ያደረገ ነው ብለዋል።
ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ እና ሩዋንዳ ድልድይ ድረስ ካለው 22.7 ኪሎ ሜትር ውስጥ ዛሬ 10 ኪሎ ሜትሩ ተመርቆ ስራ የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም 351 ሄክታር መሬት በማልማት ከ300 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል።
በተከናወነው ሰፊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታም 16 ኪሎ ሜትር የኮኔክቲቪቲ አስፋልት መንገድ፣ ከ1,000 በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግዱ 22 ፓርኪንጎች፣ 8 የኤሌክትሪክ ቻርጂንግ ጣቢያዎች፣ 18 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ፣ 22 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 5 ኪሎ ሜትር የመሮጫ ትራክ፣ 21 የልጆች መጫወቻዎች፣ 15 የስፖርት ሜዳዎች፣ 41 ድልድዮች እና 6 አነስተኛ ግድቦች ተገንብተዋል።
ይህ አጠቃላይ ፕሮጀክት ከ56 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፤ በተለይም 30 ካፌዎች፣ የመጻሕፍት ማንበቢያዎች፣ እንዲሁም በእደ-ጥበብ ባለሙያዎች 108 ሱቆች በተዘጋጁበት ሞል ውስጥ በርካታ ወጣቶችና የእደ-ጥበብ ባለሙያዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም 6 ኪሎ ሜትር የንጹህ ውሃ መስመር እና 24 ኪሎ ሜትር የድሬኔጅና ስዌሬጅ መስመር በመዘርጋት የአካባቢውን ነዋሪዎች የቀደመ ችግር መቅረፍ ተችሏል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአካባቢው ነዋሪዎች ላደረጉት ቀና ትብብር ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ፣ የተገነባው የመሰረተ ልማት የህዝብ ሀብት በመሆኑ ነዋሪው በባለቤትነት ስሜት ንጽህናውን በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲጠቀምበት ጥሪ አቅርበዋል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: