የኢትዮጵያና የቀይ ባሕር ታሪካዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ ግንኙነት በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ እጅግ መነጋገሪያ አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ ሆኖ ሰንብቷል።
ኢትዮጵያ ከተራሮቿ የሚመነጩትን ሕይወት ሰጪ ወንዞቿን ለጎረቤቶቿ ያለ ምንም ስስት በተፈጥሮ ሕግ ታካፍላለች። ይህንን የሕይወት እስትንፋስ የሆነ ውኃ የምትለግስ ሀገር ግን ከድንበሯ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የአሰብ የጨው ውኃ እንዳትነካ በታሪክ ደባ እና በጂኦ-ፖለቲካዊ አጥር ተከልላለች።
ከምፅዋ ጫፍ እስከ ሞቃዲሾ ጠረፍ የተዘረጋውን 5 ሺህ ኪሎ ሜትር የባሕር ዳርቻ በድምሩ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ይዞት ሳለ፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት እና በዓለም ላይ ትልቋ የባሕር በር አልባ ሀገር የተደረገችው ኢትዮጵያ ግን ለሕልውናዋ መተንፈሻ የሚሆን 50 ኪሎ ሜትር የባሕር በር ማጣት የተፈጥሮንም ሆነ የሰው ልጅን የፍትሕ ሚዛን የሚያዛባ ክስተት ነው።
ሰው ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል፤ ይህ የማይሻር የተፈጥሮ ሕግ እንደሆነው ሁሉ፣ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ እና ደኅንነታዊ ትሥሥር ከቀይ ባሕር ጋር የተገመደ መሆኑም የማይታበል የተፈጥሮ ሕግ ነው።
ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿን በውኃ ጥም አለመቅጣቷ የሞራል እና የተፈጥሮ ግዴታዋን ማክበሯን የሚያሳይ ከሆነ፣ የባሕር ዳርቻ ጎረቤቶቿም ከተትረፈረፈው የ5 ሺህ ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፋቸው ለኢትዮጵያ መተንፈሻ የሚሆን በር በሰላማዊ መንገድ የማጋራት ተመጣጣኝ የታሪክ እና የተፈጥሮ ዕዳ አለባቸው።
አፍሪካዊው ምሁር አሊ ማዝሩይ “ተፈጥሯዊ ያልሆነ አነስተኛ ጥገኝነት” (unnatural micro-dependency) ብለው ያነሡት ይህ የተዛባ የጂኦግራፊ እና የኢኮኖሚ ሚዛን፣ አደገኛ መዋቅራዊ ተጋላጭነትን ወልዷል።
በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ የሆነችው፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እና የቀጣናው የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው ግዙፏ ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውጭ ንግዷን የምታከናውነው በጎረቤት ጅቡቲ መሠረተ ልማት፣ የፖለቲካ መረጋጋት እና ስትራቴጂያዊ ስሌት ላይ ብቻ ተንጠልጥላ ነው።
እርግጥ ነው፣ ጅቡቲ በክፉ ቀን ለኢትዮጵያ የሰጠችው ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የጋራ መደጋገፍ የሚካድ ባይሆንም፤ ችግሩ ጅቡቲ ሳትሆን የአንድ ግዙፍ ሀገር የዓለም መውጫ እና መግቢያ በር በአንድ ኮሪደር ላይ ብቻ ሲወሰን የሚፈጠረው የብሔራዊ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ማነቆ ነው።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ማጣት እና ንግዷ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ መዞሩ ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ፣ ለንግድ መዘግየት እና ለውጭ ተጽዕኖ ተጋላጭነት እንደ ዋነኛ ማሳያ ሲሆን፣ ጉዳዩ የሕልውና ጥያቄ መሆኑን ያረጋግጣል። በመሆኑም ኢትዮጵያን ወደ ዓለም የሚወስዷት መንገዶቿ በሙሉ በሌሎች በኩል ብቻ ማለፋቸው የልጆቿን የነገ ዕጣ ፈንታ አደጋ ላይ ስለሚጥል፣ የባሕር በር ጥያቄዋን የሕልውናዋ ጉዳይ አድርጋዋለች።
ከዚህ የሕልውና ጥያቄ ጀርባ ግን ብዙም ያልተነገረለት፣ ነገር ግን በዓለም አቀፍ የሞራል እና የሕግ አደባባይ ሊመዘን የሚገባው አዲስ የንብረት ፍትሕ (Property Restitution) መከራከሪያ አለ። የኢትዮጵያ ቀደምት መሪዎች ሀገራቸውን ከባሕር ጋር ለማስተሳሰር የከፈሉት ዋጋ እና በኋላ የተፈጸሙት ታሪካዊ ስህተቶች ሲመዘኑ ይህ እውነታ ጎልቶ ይወጣል።
እ.አ.አ በ1896 ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ፈረንሳይ ከቀጣናው ስትወጣ ጅቡቲን ለኢትዮጵያ እንድታስረክብ የተፈራረሙት ውል፣ በሐምሌ 29 ቀን 1975 በካምፓላ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ በደርግ መንግሥት በይፋ መተው፤ እንዲሁም አፄ ኃይለ ሥላሴ እ.አ.አ በ1945 ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት፣ እ.አ.አ በ1947 ደግሞ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባቀረቡት ሰነድ እና እ.አ.አ በ1946 የቀረበውን የዘይላ እና የኦጋዴን የመሬት ልውውጥ ውይይት አልፈው እ.አ.አ በ1952 በፌዴሬሽን ያስመለሱትን የቀይ ባሕር መብት፣ በህወሓት የተመራው ኢሕአዴግ እ.አ.አ በ1993 ያለ ምንም የወደብ ዋስትና ለኤርትራ እውቅና በመስጠትና እ.አ.አ በታኅሣሥ 12 ቀን 2000 በአልጀርሱ ስምምነት የቅኝ ግዛት ውሎችን (uti possidetis juris) በመቀበል ኢትዮጵያን ወደብ ማሳጣቱ የታሪክ ጠባሳ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በአሰብ ላይ የገነባው ወደብ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ አውሮፕላን ማረፊያ እና አውራ ጎዳና እዚያው ቀርቷል። እ.አ.አ በ2018 የተደረሱት የሰላም ስምምነቶች ከቃል ስምምነትነት ባለመሻገራቸው ኢትዮጵያ የገነባችውን ወደብ መጠቀም አልቻለችም፤ ነገር ግን ከዚያው የ2018 እርቅ በኋላ ኤርትራውያን ከ20 ዓመታት ቆይታ በኋላ መጥተው በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ቆመው በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የነበራቸውን ቤት እና ንብረት በሕግ አስመልሰው ወስደዋል።
የግለሰቦች የንብረት መብት ከ20 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ሲከበር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት አፍስሶ የገነባውን የአሰብ ወደብ እና አውሮፕላን ማረፊያ የመጠቀም መብቱ እንዴት ሊነፈግ ይችላል? ይህ ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግ እና ፍትሕ ሊመልሱት የሚገባ ታላቅ የሞራል ጥያቄ ነው።
ይሁንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይህንን ታሪካዊ እና ሕጋዊ ቁጭት የምታቀርበው በ19ኛው ክፍለ ዘመን የግዛት መስፋፋት እሳቤ አይደለም። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ “የባሕር በር ተጠቃሚነት ግዛትን መጠቅለል አይደለም” የሚል የጠራ መስመር አስምሯል።
ስለሆነም ኢትዮጵያ እንደምትለው፣ ብልጽግናን የመጋራት መርሕ፣ የኤርትራን ምፅዋና አሰብ፣ የሶማሊያን፣ የጅቡቲን እና የኬንያን ወደቦች ከኢትዮጵያ ግዙፍ ገበያ እና የባቡር መረብ ጋር በማስተሣሠር ቀጣናውን ከጦር መሣሪያ ማስተላለፊያነት ወደ የጋራ ብልጽግና ኮሪደር የሚቀይር ብቸኛው የሰላም መንገድ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: