ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር በዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ማዕቀፍ ውስጥ የሁለትዮሽ የገበያ መዳረሻ ፕሮቶኮል ማፅደቋን የሚያሳይ የታሪክ ምዕራፍ የሆነ ስምምነት በጄኔቫ በሚገኘው የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ተፈረመ።
ይህ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የ6 አስርት ዓመታት አጋርነት የሚያጠናክርና ኢትዮጵያ ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።
በስምምነት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ጸጋአብ ክበበው፣ ስምምነቱ የንግድ ግንኙነትን ከማስፋት ባለፈ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የረጅም ጊዜ ወዳጅነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሀገሪቱ የምታደርጋቸው ማክሮ ኢኮኖሚያዊ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች አንዱ ዋና ምሰሶ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከካናዳ ጋር የተደረገው ይህ የሁለትዮሽ ስምምነትም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይል እና በሎጂስቲክስ ዘርፎች ሰፊ የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስር ለመፍጠር ትልቅ መሠረት የሚጥል ነው።
ይህ የሁለትዮሽ የገበያ መዳረሻ ስምምነት መፈረም ኢትዮጵያ ከካናዳ ጋር የነበራትን የንግድ ድርድር በስኬት ማጠናቀቋን የሚያሳይና እአአ ከኖቨምበር 9 እስከ 10, 2026 ለሚካሄደው 8ኛው የኢትዮጵያ የንግድ ድርድር የሥራ ቡድን ስብሰባ ዐቢይ ዝግጅት መሆኑ ተመላክቷል።
ስምምነቱ ለሁለቱም ሀገራት የንግድ ሥራዎች ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ እና ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓትን የበለጠ አሳታፊ እንደሚያደርገው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: