የመከላከያ ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ በኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር አብደላ ሀሰን አልሻምሲ ጋር በሁለትዮሽ ወታደራዊ እና ልማታዊ ትብብሮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ አቶ መሐመድ እድሪስ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እየሠሩ ባሉ የወታደራዊ መስኮች ላይ ያሏቸውን አጋርነቶች በማንሳት፣ የመከላከያ ሚኒስቴር በልማት ድርጅቶቹ በኩል እያከናወናቸው በሚገኙ ውጤታማ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እያደረገች ያለውን ጉልህ አስተዋፅኦ እና ድጋፍ አድንቀዋል።
አምባሳደር አብደላ ሀሰን አልሻምሲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበች ላለችው ፈጣን እና ሁለንተናዊ የልማት ዕድገት አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ስትራቴጂያዊ አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የልማት ድርጅቶች ጋር በቅንጅት መሥራት መቻላቸውን እና ለተመዘገቡት ስኬቶችም እንደ እውነተኛ ስትራቴጂያዊ ወዳጅ ሀገር የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ትልቅ ኩራት እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸው ላይ የተመሠረተ ጠንካራ የሁለትዮሽ ወዳጅነት የገነቡ መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህንን አጋርነት ወደ ላቀ እና ዘላቂ የወታደራዊ ትብብር ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት ለመሥራት መስማማታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ኦንላይን ሚዲያ የላከልን መረጃ አመላክቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: