የባሕር በር ባለቤትነትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ዙሪያ ከዚህ ቀደም የነበሩ ሥርዓቶች የተከተሏቸው የተሳሳቱ አካሄዶች ተስተካክለው አሁን ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር)፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቅ የዲፕሎማሲ ሥራ ከማከናወን ይልቅ የዚህ ተጻራሪ የሆነ አካሄድ በግልጽ መታየቱን አንስተዋል።
የመደመር መንግሥት ወደ አመራር ከመጣ ወዲህ ግን የፌዴራል መንግሥት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከሁሉ ነገር ቅድሚያ ሰጥቶ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ዶ/ር አረጋዊ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብም የመደመር መንግሥት የተከተለው አቅጣጫ ትክክለኛ መሆኑን ተገንዝቦ ከጎኑ በመሆን ሙሉ ድጋፉን እየሰጠው መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ጥረት የመደመር መንግሥት ቁርጠኝነት እና የሕዝብ አጋርነት ተቀናጅቶ ሲቀጥል ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪካዊና ሕጋዊ መብቶች የማስከበር አቅሟ የላቀ እንደሚሆን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከባሕር በር ጋር የተሣሠረ ጥንታዊ ገናና ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን አውስተው፣ ይህን የዘመናት ተሞክሮዋን መሠረት በማድረግ የጀመረችውን የባሕር ተቋሞቿን በአዲስና ዘመናዊ መልክ የማደራጀት ሂደት ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አመላክተዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: