Search

የመደመር መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ልማትን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ማክሰኞ ጥቅምት 17, 2019 54

የመደመር መንግሥት የሀገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ልማትን እና ዴሞክራሲን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

አቶ ኦርዲን ይህን ያሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምስራቅ ዕዝ በክልሉ ያስገነባውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ባደረጉበት ወቅት ነው።

ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያው የሠራዊቱን ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ተልዕኮና ለሕዝብ ያለውን የዘወትር አለኝታነት በተግባር ያሳየ ደማቅ የልማት ዐሻራ ነው።

የስፖርት ማዘውተሪያው ግንባታ መጠናቀቅ ሠራዊቱ ከወታደራዊ ግዳጁ ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያል።

ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላውና የቅርጫት ኳስ፣ የመረብ ኳስ እና የእጅ ኳስ ውድድሮችን በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ለማከናወን የሚያስችለው የስፖርት ማዘውተሪያ፤ የምስራቅ ዕዝ የሠራዊት አባላትን የውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፍላጎት ከመሙላት ባለፈ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ነው።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በምረቃው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የመከላከያ ሠራዊት የሀገር ውስጥ ባንዳ እና የውጭ ባዳን የተቀናጀ ሴራ በብቃት በመመከት ኢትዮጵያን ከማስቀጠል ባሻገር የተጣለበትን ወታደራዊ ግዳጅ በላቀ ብቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሐረር ከተማን ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እና የታሪክ ማማነቷ ለመመለስ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በምስራቅ ዕዝ ግቢ ውስጥ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ተገንብቶ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል መደረጉ፣ ከሕዝብ አብራክ የወጣው ሠራዊት በማንኛውም መከራ ውስጥ የሕዝብ እውነተኛ አለኝታነቱን ያረጋገጠበት ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።

የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት 119ኛውን የምስረታ በዓል እያከበረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ይህንን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ገንብቶ ለህዝብ ክፍት ማድረግ መቻሉ እለቱን ልዩና ታሪካዊ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።

ሰራዊቱ በአንድ በኩል የአገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት በጽናት በመጠበቅ የሚሰጠውን ግዳጅ በላቀ መስዋዕትነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸው በሌላ በኩል ደግሞ ከህዝብ ጎን በመቆም በአገራዊ የልማት ስራዎች ላይ የማገዝ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በምረቃው መርሃ ግብር ላይ የሰራዊቱ መኮንኖች፣ አባላት እና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

በቴዎድሮስ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: